የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኔዘርላንድ ሀገር ከሚገኝ “KNCV Tuberculosis Foundation” ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር በምርምርና መማር ማስተማር ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ጥር 7/2016 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሀገር ከተለዩ ስምንት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በማስፋፋትና በማጠናከር የመማር ማስተማር ሥራው ምርምር ተኮር እንዲሆን እየሠራ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዓለም አቀፍ የትብብር ሥራዎችን ዩኒቨርሲቲው በእጅጉ ይፈልጋል ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ ኮሌጁ “KNCV Tuberculosis Foundation” ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር በትብብር ለመሥራት መስማማቱ ከዩኒቨርሲቲው ትኩረት አንፃር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ ለስምምነቱ መሳካትና ተግበራዊነት እንደ ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነት መኖሩንም አክለዋል፡፡

የ“KNCV Tuberculosis Foundation” ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ጊዳዶ መስተፋ/Dr. Gidado Mustapha/ ድርጅታቸው ባለፉት 120 ዓመታት ከቲቢ እና ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎች የጸዳ ዓለምን የማየት ራዕይ ሰንቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ተግባራዊ መሆን የሚችሉና በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ የሚታይ ለውጥ የሚያመጡ ምርምሮችን ማከናወን የተቋማቸው ሥራ የጀርባ አጥንት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ጊዳዶ እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካሉ የምርምር ተቋማት ጋር የሚደረጉ ትብብሮች በሥራዎች ውጤታማነት ላይ ከፍ ያለ ልዩነት የሚፈጥሩ ናቸውም ብለዋል፡፡ የመግባቢያ ስምምነቱ ለመተግበር ተቋማቸው የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ለሁለቱም ተቋማት በእጀጉ ጠቃሚ የሆነው ይህ ስምምነት እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በበኩላቸው ከድርጅቱ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ደስታ ከአዳዲስ የምርምር አሠራር ዘዴዎች ጋር የተያያዙ የ“e-learning” ኮርሶችን ማዘጋጀት፣ ተቋማዊ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል የተመራማሪዎች ልውውጥን ማድረግ፣ ለምርምር ሥራ የሚያግዙ እንደ ቤተ-ሙከራ ያሉ ማዕከላትን ማደራጀት፣ ለሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የሚሆኑ አማካሪዎችን ማዘጋጀት፣ ከተላላፊ በሽታዎች ጋር የተገናኙ ፕሮጀክት ፕሮፖዛሎችን በጋራ ማዘጋጀት፣ ፈንድ ማፈላለግና  ፕሮጀክቶችን በጋራ መፈጸም፣ ማኅበረሰብ ተኮርና በማኅበረሰቡ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ የምርምር ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀት በስምምነቱ የተካተቱና በትብብር ተግባራዊ ከሚደረጉ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ኮሌጁ መሰል የትብብር ሥራዎች ላይ በንቃት የሚሳተፉ፣ ብቃት ያላቸው ወጣት መምህራንና ተመራማሪዎች ያሉት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደስታ ስምምነቱ መሬት ወርዶ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ኮሌጁ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በ“KNCV TB Foundation” ሲኒየር ኤፒዲሚዮሎጂስት እና የምርምር ቡድን መሪ ዶ/ር ደጉ ጀረኔ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማማከር እንዲሁም ለኮሌጁ መምህራን ስዊዲን ሀገር ከሚገኘው ለንድ ዩኒቨርሲቲ/Lund University/ ጋር በመሆን በአራት ዙሮች የተሰጠ “Complex Interventions of Pediatric Healthcare” በሚል ርዕስ ሥልጠና መስጠቱን አስታውሰው ስምምነቱ በተቋማቱ መካከል የተጀመሩ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና ለማስፋት የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የጋራ ሀብት ማሰባሰብ እና የምርምር ኮርሶችን ወይም የጋራ ምርምር ፕሮግራሞችን ማካሄድ የስምምነቱ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደጉ ቲቢን እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ አዳዲስ መፍትሄዎች ማዘጋጀት መቻል ሌላኛው የስምምነቱ ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት