የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ከጠቅላላ አገልግሎት የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በሥራ ክፍሉ በሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ተግዳራቶች፣ ጥራት ያላቸው የተሽከርካሪ መለዋወጫ ግዥ አፈጻጸም እና ሀብትን በአግባቡ ቆጥቦ በመጠቀም ዙሪያ መጋቢት 4/2016 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት ውይይቱ በሥራ ክፍሉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየት በቀጣይ ውጤታማ የሆነ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡  አያይዘውም የሥራ ክፍሉ በበቂ የሰው ኃይልና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የተደራጀ በመሆኑ የተቋሙን የሥራ መመሪያና ደንብ በአግባቡ መተግበር ከተቻለ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማሻሻል እንደሚቻል ም/ፕሬዝደንቷ አመላክተዋል፡፡

የሰው ኃብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ በበኩላቸው እንደ ሀገር ትኩረት የሚሹ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉና በለውጥ ሂደት ላይ መሆናችንን በመገንዘብ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደርን እንዲከተል በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ወጪን በመቆጠብና ገቢ የሚገኝበት አሠራር ላይ ትኩረት በማድረግ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዘመናዊ መንገድ የተሽከርካሪዎችን ደኅንነት ለመመርመርና ንጽህናቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ግብዓቶች እንዲሟሉ፣ ወቅቱንና ጥራቱን እንዲሁም ሕጋዊ የግዥ ሥርዓቱን የጠበቀ የተሸከርካሪዎች መለዋወጫ ግዥ እንዲፈጸም፣ ሚዛናዊ የተሸከርካሪዎች ስምሪት እንዲኖር እንዲሁም የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች እንዲሠጡዋቸውና በሥራ ክፍሉ ተግባብቶ የመሥራት ልምድ እንዲዳብር ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት