አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት/GIZ/ ጋር በመተባበር ለ“Forest for Future” ፕሮጀክት ግብዓት የሚሆን በ“Geographic Information System/GIS” እና በ“Global Positioning System/GPS”  ዙሪያ  ከገረሴ እና ምዕራብ አባያ ወረዳ ለመጡ 22 የደን እና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ባለሙያዎች ከመጋቢት 9 - 13/2016 ዓ/ም ድረስ ለተከታታይ 5 ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደገለጹት የሥልጠናው መሠረታዊ ዓላማ የተራቆተ መሬትን መልሶ በማገገምና ስነ-ምኅዳሩን መመለስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ የዘርፉን ባለሙያዎች  ሚና ማሳደግና ማስፋፋት ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በምድር ላይ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቆተና የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ የትምህርት ተቋማት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ይህን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የሚሄደውን የተፈጥሮ ሀብት እንዲያገግም ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ከመማር ማስተማር እንዲሁም ከምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባራት ባሻገር መሰል ሥራዎችን በመሥራት ረገድ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ ዲኑ አክለውም በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ተቋማት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ አመላክተው ሠልጣኞችም ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ተሞክሮ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲያውሉት አሳስበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር አደፍርስ ተፈራ በበኩላቸው ጂኦ ስፓሻል መረጃ የተፈጥሮ ሀብትን ለማገገም ሥራ እንዲውል ለማድረግና የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት ለመጠበቅ ያስችል ዘንድ ሥልጠና መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞችም ከሥልጠናው በኋላ ኅብረተሰቡን በማሳተፍና የተለያዩ ተቋማትን ትብብር በመጠየቅ ተጨባጭ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት የማገገም ሥራ እንደሚሠሩ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት