የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ  ጤና ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከወረዳው ጤና ጣቢያዎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች በአዲሱ የኤች አይ ቪ ምርመራ አልጎሪዝም /HIV Testing Algorithm/ እና በወባ በሽታ ሕክምናና ምርመራ አዳዲስ አሠራሮች /Malaria Technical Update/ ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ግንቦት 4/2016 ዓ/ም ተጠናቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ገብሬ በወረዳው ከሚገኙ አምስት ጤና ጣቢያዎች የተወጣጡ በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች በሥልጠናው መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ መሰል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች የባለሙያዎችን ዕውቀትና ክሂሎት ከማዳበር፣ ወቅታዊ ከማድረግ እና ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሻሻል ብሎም የተገልጋይ እርካታን ከፍ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና እንዳላቸውም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  የዚህ ዓይነት ሥልናዎችን በመስጠት ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያወሱት ኃላፊው በዩኒቨርሲቲው የሚገኘው የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ሥልጠናው እንዲሳካ ለተወጣው ጉልህ ሚና በወረዳው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ማዕከል ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ ተ/ፕ ፈለቀ ገ/መስቀል እንደገለጹት ሥልጠናው በሁለቱ የሥልጠና ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ አዳዲስ የሕክምናና የምርምራ አካሄድና አሠራሮችን ባለሙያዎች እንዲገነዘቡ የማድረግ ዓላማን ሰንቆ የተሰጠ ሲሆን በሁለት ዙሮች ከወረዳው የተወጣጡ 98 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው በዘርፎቹ የሚከናወኑ የሕክምና፣ የምርመራ እንዲሁም በሽታዎቹን የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራዎች ከዘመኑ ጋር አብረው የሚሄዱና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያግዛልም ብለዋል፡፡ የሥልጠናውን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚሰጠውን ፈተና ያለፉ ሠልጣኞች የሚሰጣቸው 15 ተከታታይ ክፍለ ትምህርቶች የያዘ የምስክር ወረቀትም ለሙያ ፈቃድ እድሳትና ለደረጃ እድገት እንደሚጠቅማቸው የማዕከሉ ኃላፊ አውስተዋል፡፡  

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኅብረተሰብ ጤና ላቦራቶሪ አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ የመጡት አሠልጣኝ ወርዛማ ባላ  በበኩላቸው የዓለም ጤና ድርጅት በገበያ ላይ ያሉ ፈጣን የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ኪቶችን ውስንነትን ከግምት በማስገባት በኪቶቹ የሚከናወኑ ምርመራዎች በቁጥር ከሦስት በማያንሱ የተለያዩ ኪቶች አልጎሪዝም ጥምረት መከናወን እንዳለባቸውና በአልጎሪዝሙ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ኪቶችም በሀገር ውስጥ ጥናት ተፈትሸውና ተገምግመው ቫይረሱ ያለባቸውን ከሌለባቸው በእርግጠኝነት የመለየት አቅማቸው እንዲሁም በተጨባጭ ከሀገራዊ የምርመራ አገልግሎት አሰጣጥ ስርጭት አንጻር ተስማሚ የአጠቃቀም ባሕርያት እንዳሏቸው ማረጋገጥ እንደሚገባ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡ በዚህም መነሻነት ሀገራት የሚጠቀሟቸውን የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ፈጣን ኪቶች አልጎሪዝም ጥምረት ከ3-5 ዓመታት ባለ ጊዜ ውስጥ ውጤታማነታቸው ከተለያዩ መስፈርቶች አንጻር ተገምግሞ ሊቀየሩ እንደሚችሉና ሀገራችንም ይህንን አሠራር እንደምትከተል አቶ ወርዛማ  ገልጸዋል፡፡ ለባለሙያዎቹ የተሰጠው ሥልጠና በሀራችን ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ኪቶች አልጎሪዝም አሠራርን ያስገነዘበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጫኖ ጤና ጣቢያ የመጣው ብርሃኑ ካሳ በሰጠው አስተያየት ሥልጠናው አዲስ ከተቀየረው የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ፈጣን ኪቶች አልጎሪዝም አሠራርና አተገባበር ጋር እንዲተዋወቅ ያስቻለው መሆኑን ተናግሯል፡፡ በቀጣይም መሰል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች በተከታታይነት ቢሰጡ ባለሙያው ከወቅታዊ የሳይንስ ግኝቶችና ከመስኩ አዳዲስ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አሠራሮች ጋር  እንዲተዋወቅ በማድረግ ለመስኩ ሥራ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ሠልጣኙ አክሏል፡፡

ከወረዳው ጋንታ ቦንኬ ጤና ጣቢያ የመጣችው ሌላኛዋ ሠልጣኝ ተረፈች ቆንጆ በበኩሏ ሥልጠናው ከዚህ ቀደም በመስኩ ያላትን ዕውቀት ከማዳበሩ ባሻገር የተሻሻሉ አዳዲስ አሠራሮችን ጭምር ያወቀችበት መሆኑን ተናግራለች፡፡ ከዚህ ቀደም መሰል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠናዎች በቀላሉ ማግኘት እንደማይቻል የገለጸችው ሠልጣኟ ይህንን ሥልጠና ላመቻቹ አካላት ሁሉ ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት