ዩኒቨርሲቲው ከቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲዎች ካውንስል ጋር የተቋማዊ ትብብር ስምምነት ተፈራረመ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲዎች ካውንስል የዩኒቨርሲቲዎች ልማት ትብብር /Flemish Interuniversity Council-University Development Cooperation (VLIRUOS) ጋር ተቋማዊ የትብብር ፕሮግራም /Institutional University Cooperation (IUC) መጋቢት 19/2009 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ይፋ አድርጓል፡፡

የትብብር ፕሮግራሙ ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ዩኒቨርሲቲው በትምህርትና ምርምር ሥራ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ መደገፍን፣ የዩኒቨርሲቲ - ኢንደስትሪ ትሥሥርና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ማጠናከርን እና በደቡብ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻሻለ የማህበረሰብ አኗኗርና ጤንነት ማረጋገጥን ዓላማ ያደረገ ሲሆን በቤልጂዬሙ ሉቨር ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት እ.ኤ.አ ከ2017-2021 ዓ.ም የሚቆይ ነው፡፡

በቤተ-መጽሐፍትና አይሲቲ ልማት፣ በግብርናና አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት፣ በአካባቢና ውኃ፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት እንዲሁም በጤና ላይ የሚያተኩሩና 72 ሚሊየን ብር የተመደበላቸው ስድስት ፕሮጀክቶች በፕሮግራሙ ተለይተው ፀድቀዋል፡፡ ከፕሮጀክቶቹ አንዱ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቤተ-መጽሐፍትና አይሲቲ አገልግሎቶችን በማዘመንና በማሳደግ የትምህርትና ምርምር ሥራዎችን ለማሻሻል ያለመ ሲሆን ቀሪዎቹ 5 ፕሮጀክቶች የደቡብ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ የማስተርስና ፒኤችዲ የትምህርት ዕድልን የሚፈጥሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት መመዘኛውን ያሟሉ 17 የዩኒቨርሲቲው ዕጩዎች በቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲዎች የፒኤችዲ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ IUC አስተባባሪ ዶ/ር ጉቼ ጉሌ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የተማሪ ቅበላና የፕሮግራሞች ቁጥርን እያሳደገ በመስፋፋት ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ፕሮግራሙ መጀመሩ የሰው ኃይል አቅሙን በዘላቂነት ለመገንባት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና፣ በብዝሃ ህይወት ጥበቃና ሌሎች ዘርፎች ወደ ህብረተሰቡ ዘልቆ ለሚያከናውናቸው በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎቶችም ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው፡፡

በኢትዮጵያ የቤልጂዬም ኤምባሲ ካውንስለርና የአምባሳደሩ ተወካይ ሚ/ር ጆሴፍ ናዶት ቤልጂዬም እና ኢትዮጵያ ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን አውስተው ይህ የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር ስምምነት በትምህርት፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት የሀገራቱን የእርስ በእርስ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ኃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የቤልጂዬም ኤምባሲ ተወካዮች፣ የኢፌዴሪ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ተወካዮች፣ የክልልና የዞን አመራሮች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ የትብብር ስምምነቱን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እና የቤልጂዬሙ ሉቨር ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ዓለም ዓቀፋዊ የተቋማት ግንኙነት ም/ኃላፊ ፕሮፌሰር ፖል ኮፒን ተፈራርመዋል፡፡ የስምምነት ፊርማውን ተከትሎ ተሳታፊዎች በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች የቤ-መጽሐፍት፣ ቤተ-ሙከራና የአይሲቲ ማዕከል አደረጃጀቶችን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ የሚገኙ በፕሮጀክቶቹ የታቀፉ ሥፍራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡