የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የአካባቢ አስተዳደርና ማህበረሰብ ትሥሥር ፎረም

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የአካባቢ አስተዳደርና ማህበረሰብ ትሥሥር ፎረም የ2009 ዓ/ም አፈፃፀምና የ2010 ዓ/ም ዕቅድ ሪፖርቱን ጳጉሜ 02/2009 ዓ.ም ለፎረሙ አባላትና ለባለድርሻ አካላት አቅርቧል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ፎረሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከተማሪ ሥነ-ምግባር፣ ከተቋም ገጽታ ግንባታና ከተማሪ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ  በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን የተቋዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ በፈቃዱ ባቀረቡት ሪፖርት ገልፀዋል፡፡

በሪፖርቱ እንደተመለከተው ተማሪዎች ከምሽት 3፡00 ሰዓት በኋላ ወደ ግቢ እንዳይገቡና እንዳይወጡ እንዲሁም አላስፈላጊ ቦታዎች በማምሸት ለተለያዩ አደጋዎች እንዳይጋለጡ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጓል፡፡ በኢኮኖሚ አቅምና በመሳሰሉ ችግሮች ክረምቱን በዩኒቨርሲቲው ያሳለፉ 32 ተማሪዎችን በማደራጀት ለእያንዳንዳቸው ብር 1007.00 በድምሩ 32,224.00 ብር ድጋፍ በማድረግ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች አካባቢ የሚታዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመቅረፍ ምቹ የመማሪያ ቦታን ለመፍጠር የተሠራ ሲሆን አደንዛዥ ዕፅ፣ ሺሻ፣ ጫትና ሲጋራ የመሳሰሉትን ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለማስገባት የሚሞክሩ ተማሪዎች በህብረተሰቡ ጥቆማና ክትትል ተይዘው የእርምት እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ሴት ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ሥልጠናዎች፣ የግንዛቤ ማሳደጊያ ብሮሸሮች፣ ተሞክሮ ማካፈያ መድረኮችና የማበረታቻ ሽልማት ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል፡፡

በአንፃሩ የተማሪዎች የሥነ-ምግባር ችግሮች፣ የመኝታ/ዶርሚተሪ/ አገልግሎት ቁጥጥር ጠንካራ አለመሆን፣ ሥርቆት፣ አደንዛዥ እፆችን መጠቀምና ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ይዞ ለመግባት መሞከር እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በተማሪዎች ላይ ንጥቂያ መፈፀም በትምህርት ዘመኑ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

ፎረሙ በ2010 የበጀት ዓመት በተማሪዎች መካከል ሊኖር ስለሚገባ የመቻቻል እሴት ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው የተማሪዎች የአለባበስና የአጋጊያጥ ሥርዓቶችን ለማስወገድ፣ በተማሪዎችና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ጤናማ ግንኙነትን ለማዳበር እንዲሁም ሴት ተማሪዎችን በመደለል ወዳልተገባ ድርጊት ለመገፋፋት የሚንቀሳቀሱ አካላትና ግለሰቦችን በመለየት ተገቢውን እርምጃ ለማስወሰድ አቅዷል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት