ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተዘጋጀ

‹‹እዚህ ደርሻለሁ፣ ቀጣዩንም እርከን በአሸናፊነት እወጣለሁ!›› በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 11/2010 ዓ/ም ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡ በፕሮግራሙ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች በቆይታቸው ሊገጥሟቸው በሚችሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ነባር ሴት ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ሴት መምህራንም ለተማሪዎች ልምድና ተሞክሮዎቻቸውን አካፍለዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ፕሮግራሙ ስለ ሥርዓተ-ፆታ መረጃ ለመስጠት፣ አርዓያ የሚሆኑ ሴት ተማሪዎችን በመሸለም አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎችን ለማበረታታት እንዲሁም ሴት ተማሪዎች በራስ የመተማመን ስሜት እንዲፈጥሩ ለማነቃቃት የተዘጋጀ መሆኑን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች አስተባባሪ ወ/ሪት አዳነች እልፍነህ ገልፀዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድህን ስኬታማ ለመሆን በራስ መተማመንና ራስን መሆን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው ሴት ተማሪዎች ከሌሎች ሴቶች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ተማሪዎች ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ውጤታማነት በራሱ የሚመጣ ሳይሆን እችላለሁ ብሎ ራስን ከማሳመን የሚጀምር ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው የትምህርት ዘመን 4 ነጥብ በማምጣት በዕለቱ ተሸላሚ ከነበሩት ሴት ተማሪዎች አንዷ የሆነችው 2ኛ ዓመት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪ ዘቢባ ሚፍታ ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች መልዕክቷን ስታስተላልፍ ተማሪዎች በምርጫቸውም ሆነ ከምርጫቸው ውጪ በሆነ የትምህርት መስክ ቢመደቡም በያዙት ጠንክረው በመሥራት ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ተናግራለች፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ባህል፣ ሐይማኖትና አመለካከት ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን በሰለጠነ ሁኔታ ችግሮቻቸውን በመፍታትና ልዩነታቸውን በማጥበብ ተቻችለው ለመኖርና የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ተቋሙ የራሳቸው መሆኑን በመገንዘብ ሊንከባከቡትና ሊጠብቁት እንደሚገባ በፕሮግራሙ ተገልጿል፡፡