ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ምክክር አካሄደ

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ከኢትዮጵያ ቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር አብሮ ለመሥራት እንዲቻል በኢንስቲትዩቱ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለመለየትና የጋራ የመግባቢያ ሠነድ (MoU) ለማዘጋጀት በሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ጥቅምት 23/2010 ዓ/ም ምክክር አካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩ በዋናነት በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ በሰው ኃይል ልማት፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ኢንተርቬንሽንና በሌሎች መሰል ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት በማለም የተዘጋጀ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንደስትሪዎችና ከአምራች ድርጅቶች ጋር በቅርበት መሥራታቸው በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡ ትምህርቶችና የሚካሄዱ ምርምሮች ከኢንደስትሪዎችና አምራች ድርጅቶች ፍላጎትና ችግሮች ጋር የተያያዙ እንዲሆኑ እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡

የቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ ደነቦ መኩሪያ በበኩላቸው ከቴክኖሎጂው ጋር እኩል ሊራመድ የሚችል ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ለዘርፉ ልማት መጎልበት  ወሳኝ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ እንደ ሀገር ያሉ እውነታዎች ላይ በቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የዘርፉ የከፍተኛ ት/ት ሥልጠና ማስፋፊያ ባለሙያ ሰነድ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ከሁለቱ ተቋማት በተወጣጡ ባለሙያዎች የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር እንደሚገባም ከስምምነት ተደርሷል፡፡ በመሆኑም የቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሥራ ድርሻዎች ተለይተው እንዲታወቁና በዩኒቨርሲቲው ያሉ የትምህርት ክፍሎችም ይህን መሠረት በማድረግ በሰነዱ እንዲካተቱ የሚፈልጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንዲያሳውቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በውይይቱ የኢንስቲትዩቱና የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡