የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዲስ አበባ ከሚገኘው የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ጋር በመተባበር ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ አዲስ አበባ ከሚገኘው የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ለተወጣጡ ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች በአነስተኛ መስኖ ምንነት፣ በመስኖ ልማት አስፈላጊነት፣ የአፍሪካ ሀገራት የመስኖ ልማት አፈፃፀም በዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ዕይታ እንዲሁም በአርባ ምንጭ ስለሚገኘው የሀሬ መስኖ ፕሮጀክትና የምርምር ሥራዎችን አስመልክቶ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የውሃ ሀብትና መስኖ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ሲሳይ ስማቸው እንደተናገሩት የስልጠናው ዓላማ በሀገሪቱም ሆነ በአፍሪካ በውሃ ሀብት አጠባበቅና መስኖን በማልማት በኩል የሚታዩ የዘርፉን ክፍተቶች በመገምገም አማራጮችን መከተል በሚገቡ ጉዳዮች የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ  በማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የውሃ ሀብት አጠባበቅና መስኖ ልማት ዙሪያ ግንዛቤን መፍጠር ነው፡፡ ስልጠናው ምሁራንን ያሳተፈ በመሆኑ ቴክኖሎጂን ያካተተ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው በውሃ አጠቃቀምና በመስኖ ልማት የጀመረውን ማህበረሰብ ተኮር ጥናት በማጠናከር  የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን  ለማረጋገጥ  ይረዳዋል፡፡

በውሃው የምርምር ዘርፍ በቂ ምርምሮችን በማድረግ ከምሥራቅ አፍሪካ ታዋቂ ከሆነውና ከአንጋፋው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የአፍሪካን ህዝብ ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ  መሠል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የዕውቀትና የክህሎት ልውውጥ ለማድረግ በዪኒቨርሲቲው በመገኘቴ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ያሉት  በዩጋንዳ ግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ኢንዱስትሪ ኢንጅነር ጀምስ ቶንዶ በኢትዮጲያ በውሃ ጥበቃና  መስኖን በማልማት ረገድ የሚታዩ ተግዳሮቶች በሀገረ ዩጋንዳም የሚታዩ ተመሳሳይ የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን ገልፀው ዩኒቨርሲቲው አበረታች ጥናቶችንና ምርምሮችን በማስቀጠል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የተጠናከረ የማኔጅመንት ሥርዓት ያለመኖር፣ ጥራት ያለው የውሃ ቦይ ዲዛይን ችግር፣ በዘርፉ በቂ ህጎች ያለመኖራቸው፣ ማህበረሰቡን ያሳተፉ በቂ የምርምር ሥራዎች አለመሰራታቸው፣ ለማህበረሰቡ መስኖን ማልማት በሚቻልበት ሁኔታ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በቂ ሥልጠናዎች አለመሰጠታቸው የመስኖ ውሃን ከመጠበቅና ከማልማት አኳያ ተግዳሮቶች መኖራቸው በስልጠናው ተዳሰዋል ፡፡

ብዙዎች ኢንጅነር ይሉኛል ኢንጅነርነት ግን ከወረቀት በዘለለ የህብረተሰቡን  ህይወት በዘላቂነት የሚቀይር ትርጉም ያለው ሥራ ሠርቶ መገኘት ነው ያሉት በኢትዮጲያ  የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ኦፊሰር ኢንጅነር ማርቲን አገር  በውሃ አጠቃቀምና በመስኖ ልማት ዘርፍ በቂ ምርምሮች ቢኖሩም ምርምሮቹ በቴክኖሎጂ የታገዙ አለመሆናቸውና ውጤታቸው አጥጋቢ አለመሆኑ የዘርፉ ፈተናዎች ነበሩ ብለዋል፡፡ ኢትዮጲያ በዘርፉ የቀረፀችው ጠንካራ የግብርና ኤክስቴንሽን ፖሊሲ ከሀገሯም አልፎ ለአፍሪካ ጥሩ ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏታል ያሉት ኢንጅነር ማርቲን በቀጣዩም የሀገሪቱን ፖሊሲ በማጠናከር  ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ የተካኑ በቂ ምሁራንን በማፍራት  የተሻለ ሊሰሩ እንደሚገባ  ጠቁመዋል፡፡ አስተባባሪው አክለው እንደገለፁት ድርጅቱ የፋይናንሻል፣ የቴክኒክና መሰል ድጋፎችን በማድረግ ለዘርፉ ጥናት የተሻለ  ይሠራል፡፡

በስልጠናው የኮንጎ፣ የሩዋንዳ፣ የኬንያ፣ የቱኒዝያ፣ ግብፅ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም የአንጎላ የዘርፉ ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ ያደረጉ ሲሆን የቱኒዝያና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምሁራን አውደ ጥናቱን  መርተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው  በውሃ ሀብት አጠባባቅና መስኖ ልማት አንፃር አበረታች ምርምሮችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ለዘርፉ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ 211 የመጀመሪያ ዲግሪና 53 የሁለተኛ ዲግሪ የውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ተማሪዎችን በዘንድሮው ዓመት ያስመርቃል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት