12ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሣውላ ካምፓስ በድምቀት ተከበረ

12ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሣውላ ካምፓስ ኅዳር 29/2010 ዓ.ም በድምቀት ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ የሀገሪቱ ህገ-መንግሥት ሲፀድቅ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ችቦ የተለኮሰበት በመሆኑ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲከበር ተማሪዎች፣ መምህራን እና የተቋሙ ማህበረሰብ ህገ-መንግሥቱ ያጎናፀፋቸውን መብቶች በመጠቀም የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህልን ለማዳበር፣ ልዩነቶችን ፍፁም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለመፍታትና ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ በሚደረገው ትግል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ልዩነቶቻችን ውበት እንጂ የግጭት መነሻ ሊሆኑ አይገባም ያሉት የሣውላ ካምፓስ ዲን አቶ ገ/መድህን ጫሜኖ ህገ-መንግሥቱ ያጎናፀፈንን መብት በአግባቡ እንዳንጠቀም ብሎም ሠላማችንን ለማደፍረስ የሚኳትኑትን ኃይሎች በአንድነት መታገል እንዲሁም ተማሪዎች በእውቀትና ክህሎት ተክነው በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈጠራና የምርምር ሥራዎች በማከናወን ለሀገራቸው የህዳሴ ጉዞ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መንግሥት የህዝቡን ጥያቄ አድምጦ ምላሽ እንዲሰጥ እና በሀገራችን ሁለንተናዊ ልማት የበኩላችንን እንድንወጣ ህገ-መንግሥቱ መሠረት የጣለ በመሆኑ ሁሌም በዓሉን ስናስበውና ስናከብረው እንኖራለን ብለዋል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የፓናል ውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የገመድ ጉተታ፣ የቁንጅና ውድድር፣ ባህላዊ ውዝዋዜ እና የማርሻል አርት ትዕይንት የፕሮግራሙ አካል ነበሩ፡፡