የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በ2010 ዓ/ም ዩኒቨርሲቲውን ለተቀላቀሉ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከኅዳር 09-10/2010 ዓ/ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት የህይወት ክህሎት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በስልጠናው የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱ ሲሆን የውሳኔ አሰጣጥ፣ የችግር አፈታት፣ ጭንቀትን የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች የጊዜ አጠቃቀም፣ የአጠናንና የፈተና አሠራር ስልቶች፣ የሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ የአባላዘር በሽታዎች እንዲሁም ያልተፈለገ እርግዝናና ውርጃ የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ሴቶች ባህላችን ከፈጠረባቸው ጫና ተላቀውና ስለራሳቸው ያላቸው አመለካከት ተስተካክሎ የሚያጋጥሟቸውን አሉታዊ የአቻ ግፊቶች መቋቋም እንዲችሉ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ራሳቸውን ከአካባቢው ጋር በማላመድ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የህይወት ክህሎት ስልጠናው የሚረዳቸው መሆኑን የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመሆናቸው ብቻ ለተለያዩ የሥነ-ተዋልዶ ችግሮች ተጋላጭ ሊሆኑ ስለሚችሉ ቀድመው መጠንቀቅና መከላከል እንዲችሉ ማስገንዘብ ተገቢ መሆኑን የሥነ-ተዋልዶ ጤና ባለሙያ የሆኑት አሰልጣኝ ስንታየሁ አበበ ገልፀዋል፡፡

ሰልጣኞቹ ሊያጋጥሟቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በቅደሚያ ትኩረት እንዲያደርጉና ራሳቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ፣ የሚየጋጥሟቸው ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ተረጋግተው የተሻሉ ውሳኔዎችን እንዲወስኑና ለትምህርታቸው እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በማስወገድ ትምህርታቸውን መቀጠል የሚችሉበትን ዘዴዎች ከስልጠናው ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው በጫሞና በኩልፎ ካምፓሶች እንዲሁም በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተሰጠ ሲሆን 2,600 ሴት ተማሪዎች ተካፍለዋል፡፡