ለደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች በመሰረታዊ የሒሳብ አያያዝ መመሪያ ላይ ስልጠና ተሰጠ

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ጎፋ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ 50 የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች በመሰረታዊ የሒሳብ አያያዝ መመሪያ ላይ ታህሳስ 4/2010 ዓ/ም  ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ኃላፊ መ/ርት ትዕግስት ኃይሌ እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ በግብር ከፋይ ነጋዴዎች ዙሪያ የሚስተዋለውን የሒሳብ አያያዝ ክህሎት ክፍተት በመቅረፍ ግብር ከፋዮች የተጣራ ገቢያቸውንና ወጪያቸውን በአግባቡ መዝግበው መረጃ በመያዝ ሪፖርት እንዲያደርጉ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም የመንግሥት ግብር ግለሰቡ ላይ እንዳይቀር ወይም ግብር ከፋዮቹ ያለ አግባብ ግብር እንዳይጨመርባቸው ሣይንሳዊ የሆነ የሒሳብ አያያዝ ዘዴን ተጠቅመው ገቢያቸውን የሚመጥን ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ ነው፡፡

ገቢ ሊያስገኙ በሚችሉ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩና በግብር ህጉ የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ የተጣለባቸው ግብር ከፋዮች የሚፈለግባቸውን የግብር ግዴታ በመወጣታቸው በዞኑም ሆነ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና ያላቸው መሆኑን ስልጠናውን የሰጡት የአካውንቲንግና ፋይናንስ ት/ክፍል መ/ር ታዬ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ የንግድ ድርጅቶች አስተማማኝ ዕድገት እንዲኖራቸውና ንብረታቸው በአግባቡ ተጠብቆና ሥራ ላይ ውሎ ተፈላጊውን ጥቅም እንዲያገኙ ዘመናዊ፣ አጥጋቢና በህግ ተቀባይነት ያለው የሒሳብ አያያዝ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል፡፡

እንደ መ/ር ታዬ ማብራሪያ ግብር ከፋዮች ተገቢውን የሒሣብ መዝገብ በመያዝ የድርጅታቸውን ገቢ እና ወጪ እንዲሁም የግብር እና የታክስ ግዴታቸውን በተመለከተ ተዓማኒነት ያለውና ሊረጋገጥ የሚችል መረጃ ሲያቀርቡ ተቀባይነቱን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ የግምት አሠራርን በማስቀረት በድርጅቱ ላይ የሚሰጡ የግብር እና ታክስ ውሳኔዎች ፍትሃዊና ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ የሚነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በሁሉም ወገን ተገቢና ተቀባይነት ያለው ምላሽ እንዲያገኙም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

የአካውንቲንግና ፋይናንስ ት/ክፍል መ/ር አቶ ብዙነህ ግርማ በሒሳብ አያያዝ ምንነት፣ በሒሳብ አያያዝ ሥርዓት፣ በመሰረታዊ የሒሳብ አያያዝ ቀመር፣ በመንትያ(የዴቢትና ክሬዲት) የሒሳብ አመዘጋገብ፣ በሒሳብ መደቦች፣ አርዕስቶችና መለያ ቁጥሮች እንዲሁም በሒሳብ መዝገብ አያያዝ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ገቢያቸውንና ወጪያቸውን በየዕለቱ መመዝገብ እንዳለባቸውና መዝገቦቹንም ሆነ የገቢ ማዘዣ ደረሰኞችን በአግባቡ በመረጃነት ማስቀመጥ እንደሚገባ ስልጠናው ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የትርፍ፣ የኪሳራ የሀብትና የዕዳ መግለጫዎችን በትክክል ሪፖርት ማድረግ እንዲችሉ የሚያበቃ ዕውቀት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ሰልጣኞች ስልጠናውን መሰረት ያደረገ ፈተና ወስደው የስልጠና ውጤት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡