የሴት መምህራንን የወደፊት የሙያ እድገት አስመልክቶ ስልጠና ተሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኔዘርላንድ ከሚገኘው NICHE ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የሴት መምህራንን ሙያ እድገት አስመልክቶ ከታህሳስ 2-3/2010ዓ/ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ ሴት መ/ራን በማንኛውም ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በማቀድ እንዲተገብሩና የተለያዩ ምርምሮችን በማከናወን ለህትመት እንዲያበቁ ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚመጡ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ለወደፊት ምን መስራትና መሆን እንዳለባቸው አስቀድመው በማቀድ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከኔዘርላንድ የመጡት Prof. Dr Sawitri saharso እንደተናገሩት የድጋፍ ሰጪ /mentor/ እና ድጋፍ ተቀባይ /mentees/ ሥርዓት አዲስ መምህራን ወደ ጥናትና ምርምር እንዲገቡ ልምድ ያላቸው መምህራን ድጋፍ የሚያደርጉበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት ማስቀጠል አዲስ መምህራን በቀጣይ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ዕቅድ ነድፈው ከነባሮቹ ጋር በመፈራረም ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡና ነባሮቹም መዋቅር አዘጋጅተው ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ያስችላል፡፡

በተጨማሪም ያገኙትን ዕውቀትና መነሳሳት በመጨመር የደጋፊውንና የድጋፍ ተቀባዩን ትስስር ወደ ተግባር ለመቀየር ዋነኞቹ ተዋናዮች ሰልጣኞቹ መሆናቸውን ፕሮፌሰሯ አክለው ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ባላቸው ጊዜና አቅም ዕቅዶቻቸውን ወደ ተግባር ቀይረው ዓላማቸውን ዳር ለማድረስና ስኬታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

ስልጠናው የተለያዩ የምርምር ተግባራትን በማከናወን ለዩኒቨርሲቲያቸውም ሆነ ለሀገራቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረላቸው መሆኑን ሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በቀጣይ ዕቅዶችን በማውጣት በርካታ ተግባራትን ለማከናወን መንገድ ከፋች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ከአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተወጣጡ 18 ሴት መምህራንና የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት ጨምሮ 8 አመራሮች በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡