የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይን በልማት ማካተት ዙሪያ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ

የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ፆታ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የሥርዓተ ፆታ ጉዳይን በልማት ማካተት ዙሪያ ታህሳስ 17/2010 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይን እንደ ዋና ጉዳይ በመመልከት በሁሉም የሥራና የትምህርት ክፍሎች በእቅድ አካቶ ከመሥራት አኳያ ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ ውጤት በሚያስገኝ መልኩ እንዲተገበርና ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ዳይሬክተሯ በየዘርፉ በሚካሄዱ የለውጥ ሂደቶች ሴቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ለማስቻል በሥራና በት/ት ክፍሎች እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም በሂደቱ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመቅረፍና ውጤታማ ለማድረግ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይን በልማት የማካተት ግንዛቤ በማስፋት የሥርዓተ ፆታ እኩልነትና ተጠቃሚነትን ለማስፈን የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሴቶችን ተሳትፎ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ስትራቴጂካዊ ግቦች ተቀምጠው በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች እንዲካተቱ በማድረግ ረገድ አበረታች ተግባራት እየተሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሥርዓተ-ፆታን በልማት የማካተት ምንነት፣ መመሪያና መገልገያ ዘዴዎች እንዲሁም ቅድመ ሁኔታዎችን የመለየትና የማጎልበት ተግዳሮቶች ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ አረጋ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በጽሑፉ እንደተመለከተው የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይን በልማት ማካተት ማለት የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይ ተቋማዊ ይዘት ኖሮት በፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች፣ ፕሮጀክቶች እና ሥራዎች ደረጃ ማካተት፤ በልማት እንቅስቃሴዎች የሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን ማስፋት፤ ክፍተት ባለባቸው መስኮች የልዩ ድጋፍ እርምጃ ተግባራዊ ማድረግና እና ሌሎችንም መሰል ተግባራት ማከናወን ነው፡፡

ሥርዓተ-ፆታን በልማት ማካተት እንደ ቁልፍ ተግባር የተያዘ ቢሆንም እምብዛም የተጠናከረ አለመሆኑ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች በእቅድ ቢያዝም ተግባራዊ ያለመሆንና ያለመጣጣም እንዲሁም ያለመተግበር እንደሚስተዋል ተገልጿል፡፡ ይህን ውስንነት ለመቅረፍ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚገባ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች የፆታ ስብጥርን በማወቅ፣ አሰራሩን በማሻሻልና ግንዛቤውን በማሳደግ ክፍተቶችን የመሙላትና የሴቶችን ተጠቃሚነት የማስፋት ሥራ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲተገበር ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በስልጠናው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የሁሉም ካምፓሶች የሥርዓተ-ፆታ አስተባባሪዎችና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡