በማዕከሉ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሄደ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ‹‹ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ስልጠና ማዕከል›› የ2010 ዓ/ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ጥር 22/2010 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ማዕከሉ በዩኒቨርሲቲው ወደ ልህቀት ማዕከልነት ከሚሸጋገሩ የምርምር ማዕከላት አንዱ መሆኑን አውስተው ለዚህም ማዕከሉን በሰው ኃይልና በቤተ-ሙከራ በማሟላት የተለያዩ ክልላዊና ሀገራዊ ተልዕኮዎቹን እንዲያሳካ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲጠናቀቅ ማዕከሉ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ጉልህ አስተዋፅዖ በማበርከት ለማህበረሰባችን የጤና ደረጃ መሻሻል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ላይ ምርምሮችን ማካሄድ፣ የመድኃኒት ሥርጭት ቁጥጥር ማድረግና ደረጃውን የጠበቀ ሞጁል አዘጋጅቶ ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠት የማዕከሉ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ገዝሙ ተናግረዋል፡፡ በሀገር ውስጥ እስከ አሁን በመድኃኒት ስርጭትና ቁጥጥር ዘርፍ የተሰራውን በመለየት እንደዚሁም የጤና ጥበቃ የትኩረት ጉዳዮችን ከግንዛቤ በማስገባት በሚታዩ ክፍተቶች ላይ ለመሥራት የሚያስችሉ የምርምር ፕሮፖዛሎች በማዕከሉ ይዘጋጃሉም ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ማዕከሉ UK ከሚገኘው (DFID – Department for International Development) ድርጅት ከ750,000.00 - 100,000.00 የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ የሚያስገኙ ሁለት የተግባር ምርምር ፕሮፖዛሎችን አዘጋጅቷል፡፡

የሆድ ጥገኛ ትላትሎች ህክምና ማሻሻያ፣ በጋሞ ጎፋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የእከክና የሙጀሌ በሽታዎች ተጠቂ ሰዎች ቁጥርና የበሽታዎቹ የመባባሻ ምክንያቶች እንዲሁም የተጠናከረ የትራኮማ በሽታ መድኃኒት ቢኖርም የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣበት ምክንያት በሚሉ 3 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተግባር ምርምር ፕሮጀክቶች ተቀርፀው የተተቹ ሲሆን ወደ ትግበራ ለመግባት አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀረበው የዕቅድ ክንውን ሪፖርት እንደተመለከተው ማዕከሉ ለ4ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ትግራይ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚካሄደው የተናጥል መድኃኒት ሥርጭት ቁጥጥር ሥራ ዝግጅት ያጠናቀቀ ሲሆን ከአጋር ድርጅቶች ጋርም የትብብር ውል ስምምነት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በ2,266,840.00 ብር በጀት 13 ገምጋሚዎችና 48 ተቆጣጣሪዎችን በማሳተፍ በ24 ወረዳዎችና የበሽታዎቹ ምልክቶች በታዩባቸው 144 የተመረጡ ጣቢያዎች  የሥርጭት ቁጥጥሩ የሚከናወን ይሆናል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ካሉ ሌሎች የሥራ ክፍሎች፣ በቅርበት ከሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጤና ተቋማት፣ ከዞናዊና ክልላዊ ቢሮዎች ጋር በጋራ መስራት፣ የኮሌጁን የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች አቅም መገንባት፣ የዩኒቨርሲቲው ህብረተሰብ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ግንዛቤ መፍጠር እና ማዕከሉን ለማጠናከር ሥራዎችን በመገናኛ ብዙሃን  ማስተዋወቅ የተጀመሩ ተግባራት ሲሆኑ ማዕከሉ በቀጣይ በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡

ማዕከሉ የማህበረሰቡን ጤናና ሕይወት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን፣ የምርምር ሥራዎችን ማካሄድና የሕክምና ተማሪዎች የምርምር ሥራዎችን መደገፍ፣ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ስልጠናዎችን ማስተናገድና ማመቻቸት እንዲሁም የሚሠሩ ተግባራትን የተመለከተ ተገቢ የመረጃ ልውውጥና የተግባቦት ሥራ በማከናወን የማዕከሉንና የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ መገንባት እንዳለበት በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና እና ኢፒዲዮሞሎጂ ዘርፍ አማካሪ ዶ/ር አያና የኔአባት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን ለሌሎች ተቋማትም አርአያ ሊሆን ይገባል፡፡ የሙሉ ጊዜ ተመራማሪዎች (full time researchers) እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡