ዩኒቨርሲቲው ለሴት መምህራን፣ 2ኛ ዲግሪ ላላቸው ሴት የአስተዳደር ሠራተኞች እና የ2ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ላሉ ሴት የአስተዳደር ሠራተኞች ከመጋቢት 13-15/2010 ዓ.ም በምርምር ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬትና የምርምር ዳይሬክቶሬት በመቀናጀት ያዘጋጁት ስልጠና በምርምር ምንነትና አስፈላጊነት፣ በምርምር ፕሮፖዛል አዘገጃጀት፣ በልማት ዕቅድ (Development project) አዘገጃጀት፣ በዳታ አናሊሲስ (data analysis) እንዲሁም በ STATA ሶፍትዌሮች አጠቃቀምና ትንተና ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ት ሰናይት ሳህለ በስልጠናው ወቅት እንደተናገሩት በዓለማችን በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተሳትፎ አብላጫውን ቁጥር የያዙት ወንዶች ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲውም የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር ጥቂት በመሆኑ ሴቶች እውቀትና ክህሎታቸው ዳብሮ እና ተነቃቅተው በዘርፉ የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆኑ ስልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

ሴቶች ሣይንሳዊ ምርምር ለመሥራት በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው እና የሴት ተመራማሪዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ስልጠናው አስፈላጊ መሆኑን የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ የሳይንሳዊ አርቲክል አጻጻፍ (scientific manuscript writing) ዘዴዎችን አውቀው ደረጃቸውን የጠበቁ ምርምሮችን በማካሄድ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እንዲያሳትሙ ያስችላቸዋል፡፡

በሃይድሮሎጂ 2ኛ ዲግሪዋን በመከታተል ላይ የምትገኘው ሰልጣኝ ማርታ ምርቴ ስልጠናው ለምትሠራው ጥናትና ምርምር ከርዕስ ጀምሮ የሚካተቱ ነጥቦችንና የሶፍትዌር አጠቃቀምን ያካተተ በመሆኑ የተሻለ ግንዛቤ ስለፈጠረላት መደሰቷን ተናግራለች፡፡

ከዚህ ቀደም መሠረታዊ የሶፍትዌር ዕውቀት ቢኖረኝም በስልጠናው ተጨማሪ ክህሎት አግኝቻለሁ ያለችው ከኢኮኖሚክስ ት/ ክፍል የመጣችው ሰልጣኝ አምሳል ተክሌ መሰረታዊ የጥናትና ምርምር ክህሎቶችን ጠለቅ ባለ ሁኔታ ማየታችን  ቀጣይ የምንሠራውን  ምርምር እንድናጠናክር ያግዛል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

የሲቪል ምህንድስና ት/ክፍሏ ሰልጣኝ አባዲ ወይና በበኩሏ ከዚህ ቀደም በሶፍትዌሮች ዙሪያ ስልጠና ወስዳ አለማወቋን ተናግራ ስልጠናው አቅሟን እንድትፈትሽ ማድረጉን ገልፃለች፡፡ በተለይ ሁሉም የምህንድስና ተማሪዎች ሊያውቋቸው የሚገባቸውን ሶፍትዌሮች ስላካተተ በቀጣይም ትኩረት ተሰጥቶ  ቢሰጥ በምርምሩ ዘርፍ በቂ ክህሎት ያላቸውን ሴት ተመራማሪዎችን ለመፍጠር ያስችላል ብላለች፡፡