የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ቢሮ ከጋሞ ጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ጋር በመሆን ለአካባቢ ጥበቃ አጋዥ የሚሆኑ አበረታች ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በዚህም ረገድ ከዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ቢሮና ከዞኑ ግብርና ቢሮ የተወጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በጋሞ ጎፋ ዞን በቦንኬ ወረዳ ካሻ ኬሻሶ ቀበሌ በሚገኝ የችግኝ ጣቢያ ግንቦት 11/2007 .ም ጉብኝት አካሂዷል፡፡ የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በአካባቢው የሚገኙ የተራቆቱ መሬቶች በሥነ-ህይወት ሥራ መልሰው እንዲያገግሙ፣ የተፋሰስ መሬቶች በውኃ ታጥበው እንዳይወሰዱ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ በተለያዩ የጥላ፣ የመኖ፣ የውበትና የፍራፍሬ ችግኞ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

ማስተባበሪያ ቢሮው ከዚህ ቀደም በምዕራብ አባያ ወረዳ በሚገኙ ሁለት ቀበሌያት ያሉ የችግኝ ጣቢያዎችን ደረጃ ከማሻሻል አንፃር የቁሳቁስ፣ የሙያና የሰው ኃይል ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ በሚገኙ የተራቆቱ ቦታዎች እንዲሁም በአጎራባች ቀበሌያት ከ1ሺ ሄክታር በላይ መሬት በመከለል፣ የተለያዩ አካላዊና ስነ-ህይወታዊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንዳለ የቢሮው ኃላፊ አቶ ደረጀ ኤልያስ ገልፀዋል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን ግብርና ቢሮ የአፈር ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ውብሸት ዘውዴ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው እየተከናወነ ያለው ሥነ-ህይወታዊ ተግባር የአካባቢውን መሬት በመጠበቅና ለነዋሪዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሰፋ የሚያደርግ ነው፡፡

በተመሳሳይም በቅርቡ በምዕራብ አባያ ወረዳ በአራት ቀበሌያት ከዞን ግብርና መምሪያ ፣ ከምዕራብ አባያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤትና ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመሆን የቀመ-ራያ ተፋሰስን ለማልማት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡