የዩኒቨርሲቲው የኮሚዩቲ ትምህርት ቤቶች የወላጆች ቀን በዓል ሰኔ 28/2007 /ም በዩኒቨርሲቲው የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

የትምህርት ቤቶቹ ዋና ርዕሰ መምህር አቶ ጌታቸው አስፋው ትምህርት የዜጎችን የችግር ፈቺነት አቅም በማጎልበት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማስረጽና የሰው ልጅ አካባቢውን በሚገባ አጥንቶ እንዲጠቀም በማድረግ ረገድ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚኖረው ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ጌታቸው የትምህርት ዘመኑን ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት ሲያቀርቡ በሦስቱም ት/ቤቶች በመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ፣ በትምህርት ግብዓትና አደረጃጀቶች፣ በፋይናንስና በጀት አጠቃቀም፣ በመምህራንና በተማሪዎች ሥነ-ምግባር እንዲሁም በሌሎች አበይት ክንውኖች ላይ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡ በትምህርት ዘመኑ ፈታኝ ሂደቶች ቢኖሩም ከመምህራንና ሠራተኞች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች ጋር በቅንጅት በመሠራቱ በብቃት መወጣት መቻሉን ርዕሰ መምህሩ በሪፖርታቸው አውስተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንትና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ጉቼ ጉሌ በት/ቤቶቹ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት መልካም ዜጋ ከመፍጠር አኳያ የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል የተማሪ ወላጆች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ በ2008 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶቹን አደረጃጀት በማሻሻልና ደረጃ በማሳደግ የመሠናዶ ትምህርት ለማስጀመር መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ በሦስቱም ትምህርት ቤቶች ከመዋዕለ ህፃናት እስከ 10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በዓመቱ ሲከታተሉ የነበሩ 775 ተማሪዎችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አካላት፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ የተማሪ ወላጆች እና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን በተማሪዎች የተዘጋጁ የስነ-ጹሑፍ ሥራዎች፣ ድራማዎችና ሌሎችም ትዕይንቶች የበዓሉ ልዩ ድምቀት ነበሩ፡፡

በበዓሉ ማጠቃለያ ላይ በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተማሪዎች ፣በዓመቱ መልካም አፈፃፀም ለነበራቸው የትምህርት ቤቱ መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡