አለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ ፡፡

የአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት / wmo/ ከተቋቋመበት እ..አ ከ19 50 ዎቹ ጀምሮ አለም አቀፍ የሚቲዮሮሎጂ ቀን በየዓመቱ መጋቢት 14 / March 23 /የሚከበር ሲሆን በዚህ ዓመት “Climate knowledge for climate action በሚል መሪ ቃል በአ//ዩ በተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ በፓናል ውይይትና በችግኝ ተከላ ተከብሯል ፡፡

የሚቲዎሮሎጂ ቀን ተማሪዎችና መምህራን የወቅቱን የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የባህር ነውጦችን መንስኤ በማጥናት በተለይ አርሶ አደሩ በቂ ድጋፍና ግንዛቤ የሚያገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት ግኝታቸውን የሚያስተላልፉበት አጋጣሚ መሆን እንዳለበት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አጌና አንጁሎ ተናግረዋል ፡፡

የበዓሉ ዋነኛ ዓላማ በሰው ልጆች የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የሚፈጠረውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን ለማሳደግ ከሳይንሱ ጋር የተያያዙ መረጃዎችንና እውነታዎችን ማስጨበጥ እንደሆነም የሚቲዎሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ሙሉጌታ ገናኑ ገልፀዋል ፡በተጨማሪም መምህሩ በሚቲዎሮሎጂ ትምህርት ክፍል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በዝርዝር አቅርበዋል ፡፡

የሚትዎሮሎጂ ትምህርት ከሁሉም የሳይንስ ትምህርቶች ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ዓለም አቀፋዊ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን በጤና ፣በአካባቢ ጥበቃ ፣በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የትምህርት ክፍል ነው፡፡ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ኃ/ሚካኤል ፕሮግራሙን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት በዕለቱ የተነሱት ጉዳዮች የሰዎችን ግንዛቤ ከማስፋት አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸውና አስተማሪ መሆናቸውን በመግለፅ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሚደረጉ ጥናትና ምርምር ስራዎች ጎን ለጎን ኮሌጁ በእለቱ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

 

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

//