ስምንተኛው ዙር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና በደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ተካሂዷል፡፡

ሻምፒዮናው የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሽመልስ ታደሰ ለተሳታፊ ስፖርተኞችና እንግዶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተጀመረ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች ጠንካራ ፉክክር የታየበትና የብዙ ተመልካቾችን አድናቆት ያገኘ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ለሁለት ሣምንታት በቆየው ሻምፒዮና በሴቶች ቅርጫት ኳስ የደቡብ ፣የአማራና የትግራይ ክልሎች የተሳተፉ ሲሆን የአማራ ክልል ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ በወንዶች ቅርጫት ኳስ ተሳታፊ ከነበሩት የደቡብ፤ የአማራ፤ የሐረሪ፤ የድሬዳዋና የትግራይ ክልሎች መካከል አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ የደቡብ ክልል ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በክለብ ደረጃ በሴቶች የመንግስት ቤቶች ኤጄንሲ የቢጂአይ ኢትዮጵያ አቻውን ሲያሸንፍ፤ በወንዶች የውኃ ሀብት ልማት ሥራዎች የፌደራል ፖሊስ እና የኦሎምፒያስ ቅርጫት ኳስ ክለብን በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡

ውድድሩን ይበልጥ ማራኪና ተወዳጅ ለማድረግ በአዘጋጆቹ ዕውቅና ዕድል የተሰጠው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቅርጫት ኳስ ቡድን የኦሎምፒያስ አቻውን በመግጠም በጠባብ ውጤት ተሸንፏል፡፡

በሻምፒዮናው ፍጻሜ ፌዴሬሽኑ ለአስተናጋጆቹ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምስጋና የምስክር ወረቀት እና የዋንጫ ሽልማት የሰጠ ሲሆን በወቅቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ሽልማትና የምስክር ወረቀቱን ተቀብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን አባላት በሰጡት አስተያየት በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነትና በመቻቻል የተካሄደው ሻምፒዮና ባለፉት ጊዜያት ከተካሄዱት ወድድሮች ይበልጥ ማራኪ መሆኑን ገልፀው በዩኒቨርሲቲው ውብ ጂምናዚዬም መካሄዱ ለጨዋታው ልዩ ድምቀት ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ውድድሩን በማስፈጸምና በቂ የመወዳደሪያ ሥፍራን በማመቻቸት እንዲሁም ተሳታፊ ቡድን እንግዶችን በመቀበል በኩል የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ የጎላ ሚና እንደነበረው ዶ/ር ቾምቤ አናጋው የአካዳሚው ዳይሬክተር ገልጸዋል ፡፡

በሻምፒዮናው ከአምስት ክልሎች እና አባል ክለቦች የተወጣጡ ከ500 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡