ዩኒቨርሲቲው ከፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችና አፈፃፀሞች እንዲሁም በተቋማዊ የለውጥ ትግበራ ሥራዎች ላይ ከመስከረም 27/2008 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ Click here to see the Pictures.

 

የሥልጠናው ዓላማ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱ ሠላማዊ እንዲሆንና ተማሪዎች በሀገሪቱ ስለተመዘገቡ ስኬቶችና ስላጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም ለወደፊቱ ስለሚጠበቁ ስራዎች ግንዛቤ ኖሯቸው የበኩላቸውን ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ስለ ዩኒቨርሲቲው በቂ መረጃ ይዘው በትምህርታዊና ተቋማዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑም ያስችላል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ የትምህርት ጥራት የማስጠበቅ ሥራና የባለድረሻዎች ሚና፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማዊ ለውጥ ትግበራ ሥራ የደረሰበት ደረጃ፣ ቀጣይ ጉዳዮችና የአመራሩ ሚና፣ ሕገ መንግስታዊ መርሆዎችና ሰላማዊ የትግል ስልት በትምህርት ተቋማት፣ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት የሴኩላሪዝም መርሆዎችና የመንግስት አካላት ሚና ፣ የሀይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት አደጋና የመታገያ ስልቶች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የ2008 ዓ.ም ዕቅድ በሥልጠናው የተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያዎችና መረጃዎችም በተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር፣ በየኮሌጆችና በኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎች ተሰጥተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባሉት አንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና አምስት ኮሌጆች በ49 የቅድመ-ምረቃና በ40 የድህረ-ምረቃ የትምህርት ዘርፎች 5,784 አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ተዘጋጅቷል፡፡