ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ በትምህርት ክፍል፣ በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከመምህራንና ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ በተመረጡ 14 የትኩረት መስኮች ምርምሮች እየተከናወኑ መሆኑን የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን ወ/ሰንበት እንደገለጹት የምርምር ሥራ ችግሮችን ከመነሻቸው በማጥናት ተገቢነት ያለው፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚረዳ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በዋነኛነት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህም ዩኒቨርሲቲው በ2007 ዓ/ም የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በአካባቢያቸው በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ በሰጡት አስተያየት መሠረት 90 ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
ዶ/ር ፋንታሁን በያዝነው ዓመትም የተጀመሩ የምርምር ስራዎችን የማስጨረስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዉ  ከተለያዩ የውጭ ሀገራት አጋሮች ጋር በመቀናጀት በእንሰት፣ በአፕልና በውሃ ላይ ምርምሮች እየተካሄዱ ናቸዉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በ‹‹ታላቁ የኩልፎ ፕሮጀክት›› የጫሞ ሐይቅን እየሞላ ያለውን ደለል መነሻ ለማወቅ በአካባቢ ምልከታና ማህበረሰቡን በማነጋገር የችግሩን ምንጭ የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው ፡፡ ሌሎች አዳዲስ የምርምር ስራዎችን የማስጀመር፣ የምርምር  ግብዓቶችን የማሟላትና የምርምር ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል፡፡
በተጨማሪም በህዋ ሳይንስ ዙሪያ ለሚደረገው ጥናት ቅድመ ጥናትና የአዋጭነት ጥናት ማድረግ፣ በ2ኛው የዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አለም አቀፍ ፣አህጉር አቀፍና አገር አቀፍ ተቋማት ጋር የጋራ ፕሮፖዛሎችን በማዘጋጀት ፕሮጀክቶችን መጀመርና ገቢን ማሳደግ፣ የመምህራንና ተማሪዎችን ክህሎት ማሳደግ እንዲሁም የመረጃ አያያዝ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የመረጃ ቋት ማዘጋጀት በዕቅድ ተይዘዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ጆርናሎችን ለማህበረሰቡ በተለይም ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግና ደረጃቸውን የጠበቁ ላብራቶሪዎች ለመገንባትም ቅድመ ዝግጅቶች ይደረጋሉ፡፡
የሴት ተመራማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ ነባር ተመራማሪዎችን በማበረታታትና አዳዲስ ተመራማሪዎችን በመቅጠር ወደ ምርምር ሥራ የማስገባት እንዲሁም የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የመመረቂያ ፅሁፋቸውን በዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮች ላይ እንዲሰሩ የታቀደ ሲሆን የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን በማወዳደር ከየትምህርት ክፍሉ አንድ አንድ ፕሮፖዛሎችን መስሪያ የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል፡፡