የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ከአ/ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል ጋር በመተባበር “አካል ጉዳተኛን ማካተት ወሳኝ ነው፤ ተደራሽነትና ማብቃት ለሁሉምˮ በሚል መሪ ቃል ዓለም ዓቀፉን የአካል ጉዳተኞች ቀን በ21/04/08 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው አክብሯል፡፡ የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጳውሎስ ታደሰ የልዩ ፍላጎት አገልግሎት የ2008 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው 53 ነባርና 18 አዲስ ገቢ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ ለተማሪዎቹ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ ማደሪያ፣ ቤተ-ሙከራ፣ መማሪያ፣ መመገቢያ ክፍሎች፣ ክሊኒክ እና ቤተ መጽሐፍት ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በ2007 ዓ.ም የተቋቋመው የአካል ጉዳተኞች ሪሶርስ ማዕከል GIS እና AutoCAD ሶፍትዌሮች የተጫኑባቸውና የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ 20 ኮምፒውተሮች ተሟልተውለታል፡፡ ማዕከሉ ወቅታዊ የህትመት ውጤቶች/ጋዜጦችና መጽሔቶችን/ የያዘ ሲሆን የአጠቃቀም መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ማጣቀሻ መጽሐፍትን ማሟላት፣ የICT ሥልጠና መስጠት፣ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ መጸዳጃ እና ሻወር ቤቶችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ማድረግ በዕቅድ የተያዙ ሥራዎች ናቸው፡፡ ምቹ አካባቢ ከመፍጠር አኳያም ነባር፣ በግንባታ ላይ ያሉ እና ወደፊት የሚገነቡ ህንፃዎችና መንገዶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
የአርባ ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታፈሰ ጭርቦ ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ እንደተገለጸው በታዳጊ ሀገራት 115 ሚሊየን ህፃናት የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ዕድልን አላገኙም፡፡ ከእነዚህም መካከል 40 ሚሊየን ያህሉ አካል ጉዳተኞች ሲሆኑ 80 በመቶ አካል ጉዳተኞች በታዳጊ ሀገራት ይገኛሉ፡፡ በዓለም ባንክና በዓለም ጤና ድርጅት የ2011 ሪፖርት መሠረት 17.6 በመቶ (16 ሚሊየን) ያህሉ ኢትዮጵያዊያን አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡ ይህም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ ሰብዓዊ መብት የሆነውን ትምህርት በፍትሀዊነት ለማዳረስ ከታችኛው ደረጃ ጀምሮ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ ያሳያል፡፡
ተሀድሶ ማዕከሉ ለአካል ጉዳተኛ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዊልቸር፣ ክራንች፣ አርቲፊሻል እግር የሚያገኙበትን ዕድል ያመቻቻል፡፡ በ2008 ዓ.ም ECDD/Ethiopian Center for Disability and Development/ የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም የፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ፕሪንተር እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ለተመራቂ ተማሪዎች Carrier Development Training በመስጠት የልምምድና የሥራ ዕድል ያመቻቻል፡፡
የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት የማኅበረሰቡ አንድ አካል የሆኑ አካል ጉዳተኞችን የማግለል ችግር እንደነበር ገልፀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ በከፊልም ቢሆን ተቃሎ አካል ጉዳተኞች ትኩረት ለማግኘት ችለዋል፡፡ በዚህ ረገድም ዩኒቨርሲቲው የሚፈለገውን ያህል አከናውኗል ባይባልም አበረታች ጅምሮች በመኖራቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት