ዩኒቨርሲቲው በህክምና ዶክትሬት 47 እንዲሁም በስነ ህንጻና ከተማ ፕላን 57 በድምሩ 104 ተማሪዎች የካቲት 26/2008 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ብቁ ተማሪዎችን በማፍራት የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፈ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

ተመራቂዎች የሙያ ሥነ ምግባርን በመላበስ የሀገራቸውን ራዕይና ግቦች ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ያሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና  የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ናቸው፡፡

ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ዶ/ር ደሳለኝ መቻል፣ ዶ/ር ሮዳስ ተመስገንና ዶ/ር ሽመልስ ጌቱ ከህክምና ት/ቤት፤ ምሩቅ ተማሪ ሻውል ጉልላት፣ ሰለሞን ታምሩና ዮናስ ኪዳነማርያም ከስነ ህንጻና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል በቅደም ተከተል ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ተሸልመዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በሰለጠኑበት መስክ የሙያው ሥነ ምግባር በሚፈቅደው መልክ ህብረተቡን በታማኝነት ለማገልገልና የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የህክምና ተማሪዎችን ለሁለተኛ ጊዜ የስነ ህንጻና ከተማ ፕላን ተማሪዎችን ደግሞ ለስምንተኛ ጊዜ ያስመረቀ ሲሆን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የትምህርት ፕሮግራሞቹን በማሳደግ የቅደመ ምረቃን 66 እንዲሁም የድህረ ምረቃን 40 ለማድረስ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡