ለደቡብ ኦሞ ዞን ማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና ሰራተኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከህግ ት/ቤት ጋር በመተባበር በደቡብ ኦሞ ዞን ለሚገኙ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና ሠራተኞች በመሰረታዊ የታራሚዎች መብትና አያያዝ ሰኔ 10/2008 ዓ.ም የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የስልጠናው ዓላማ የታራሚዎችን የሰብአዊ መብት ጥበቃ የተሻለ ለማድረግ በወጡ ሀገር ዓቀፍና ዓለም ዓቀፍ ህጎች ላይ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና ሰራተኞችን ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም ታራሚዎች መሰረታዊ መብቶቻቸውን እንዲገነዘቡ ማድረግ መሆኑን የህግ ት/ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ገልፀዋል፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ታዬ በበኩላቸው በማወቅና ባለማወቅ በተለያዩ መንገዶች በታራሚዎች ላይ የህግ ጥሰቶች የሚከሰቱ በመሆኑ ስልጠናው ታራሚዎች መብታቸውን እንዲያውቁ እንዲሁም የህግ አስከባሪዎች የታራሚዎችን መብት ሳይጋፉ ህግን እንዲያስከብሩ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የሥልጠና ሰነዱ በህግ ት/ቤት መምህር አቶ ራህመቶ ሲርጋጋ የቀረበ ሲሆን መሰረታዊ የታራሚዎች መብትና አያያዝ፣ ዋና ዋና ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ህጎች፣ የማረሚያ ቤቶች ዓላማና ደንቦች እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ ሴትና አካል ጉዳተኛ ታራሚዎች የሚሉ ርዕሶችን አካቷል፡፡ የአካል ደህንነት፣ ከኢ-ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸውና ከህግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘት የመሳሰሉ በፍርድ ቤት ያልታገዱ በጥበቃ ስር ያሉ ታራሚዎች መሰረታዊ መብቶች ላይም ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ነፍሰ ጡርና አራስ ታራሚዎች በህክምና ባለሙያ ትዕዛዝ ተጨማሪ ምግብ ሊቀርብላቸው እንደሚገባ እና በማረሚያ ቤቶች የሚገነቡ ህንፃዎች፣ የንጽህና ቤቶችና የመኝታ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኞችን ከግንዛቤ ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው በሥልጠናው ተገልጿል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያያት ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ እና የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁ ሥልጠናው በቂ ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው ገልፀዋል፡፡ ታራሚዎች ታንጸው፣ ተለውጠውና የተለያዩ ሙያዎችን ቀስመው ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ራሳቸውንና የበደሉትን ህብረተሰብ በልማት እንዲክሱ ለማመቻቸት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ከዞኑ ማረሚያ ቤት እና ከወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤቶች የተወጣጡ ከ40 በላይ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና የፖሊስ አዛዦች ተሳትፈዋል፡፡