ዓለም ዓቀፉ የነጭ ሪባን ቀን "በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ጥቃቶችን በመከላከልና በማስቆም የዕድገትና የህዳሴ ለውጥ ዘላቂነትን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ቃል በዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ታኅሣሥ 04/2009 ዓ.ም በዋናው ግቢ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ በዓሉ ሲከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በሀገር ደረጃ ደግሞ 11ኛ ጊዜ ነው፡፡

የነጭ ሪባን ቀን በየዓመቱ ከህዳር 16 - 30 ወንዶች ነጭ ሪባን በደረታቸው ላይ በማድረግ ''ጥቃት አላደርስም፤ ሲያደርሱም አይቼ ዝም አልልም፤ ተባባሪም አልሆንም'' በማለት በሴቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ ቃል የሚገቡበትና ጥቃት የሚያደርሱትንም በማውገዝና ከሴቶች ጎን በመቆም አጋርነታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ መሆኑን የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ገልፀዋል፡፡

የሀገሪቱን እድገትና ህዳሴ ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ለሆኑት ሴቶች እድገትና ደህንነት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ሴቶች ላይ የሚደርሱ ተጽዕኖዎችንና ጥቃቶችን ለመከላከል የተሻለ ግንዛቤ በመያዝ መታገል እንደሚገውም አጽኖት ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የነጭ ሪባን ቀን አከባበር፣ የሴቶች መብት ጥሰት፣ ከሴቶች ጥቃት ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ህግጋት፣ ከህግና ከሰብዓዊ መብት አንጻር የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎችና ሴት ሠራተኞች ላይ በሚደርሱ ጾታዊ ትንኮሳና ያልተገቡ ባህሪያት  የዩኒቨርሲቲው የውስጥ ህገ ደንብ አፈፃፀም ላይ በሥርዓተ ፆታ ባለሙያዎችና በሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ት/ክፍል ባለሙያዎች ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ጾታዊ ትንኮሳና ሌሎች በሴቶች ላይ በትምህርትም ሆነ በሥራ አጋጣሚ ሊደርሱ የሚችሉ ተጽኖዎችን በሚመለከት ግንዛቤ የመፍጠርና ክትትል የማድረግ ሥራ የተጠናከረ እንዳልሆነ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲቻል ሁሉም  የዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ  በቅንጅት መንቀሳቀስ እንደሚኖርበትም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከል የማህበረሰቡን ግንዛቤ በስልጠናና በሌሎችም መንገዶች ከማሳደግ ባለፈ በሴት ተማሪዎችና በሴት ሰራተኞች ሊደርሱ በሚችሉ ጾታዊ ትንኮሳና ያልተገባ ባህሪ ላይ የውስጥ ህገ ደንብ ተዘጋጅቶና በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ፀድቆ ተፈፃሚ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በአፈፃፀም ረገድ የሚታዩ ውስንነቶችን በጋራ መፍታትና የሚከሰቱ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለማስወገድ መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ከሁሉም ካምፓሶች የተጋበዙ ሴት መምህራንና ሠራተኞች፣ ተማሪዎችና ሌሎችም እንግዶች የታደሙ ሲሆን ዕለቱን በማስመልከት በተማሪዎች የተዘጋጁ ግጥሞችም ቀርበዋል፡፡