ዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዙር የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ

ዩኒቨርሲቲው በህክምና ዶክትሬት ያሰለጠናቸውን 46 የህክምና ዶክተሮች ህዳር 17/2009 ዓ.ም በድምቀት አስመርቋል፡፡

ከተመራቂዎቹ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ዶ/ር ተመስገን እንዳለው የወርቅ ሜዳልያ ተበርክቶለታል፡፡ ዶ/ር ዳንኤል ታምራት እና ዶ/ር አብዱልፈታ መሐመድ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ሲሸለሙ ዶ/ር ጫልቱ ኔሞምሳ 3.03 በማምጣት ብቸኛዋ ሴት ተመራቂና ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት በሀገሪቱ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል የማፍራት ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን የዘንድሮዎቹን የ3ኛ ዙር ምሩቃን ጨምሮ 131 የህክምና ዶክተሮች አሠልጥኖ በማስመረቅ ለህክምናው ዘርፍ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ከምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት የህክምና ትምህርት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን አጽንኦት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ እንዲያደርግ ፕሬዝደንቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አሚር አማን እንደገለጹት የህክምና ዶክተሮችን የማስተማር የቅበላ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ እንዲሁም ከ36 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት ከ100 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች በሀገሪቱ ቢኖሩም የጤናው ዘርፍ አሁንም በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል፡፡ ለዓብነትም በየዓመቱ ከ11 ሺህ በላይ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ይሞታሉ፤ ከ20 ህፃናት አንዱ 5 ዓመቱን ሳያከብር ይሞታል፤ ከ14 ህፃናት አንዱ ደግሞ አንድ ዓመት ሳይሞላው ይሞታል፡፡

ሙሉ ሀኪም ለመሆን ዕውቀት እና ክህሎት በቂ ባለመሆኑ በመልካም ስነ-ምግባር በመታነጽ ተገልጋዩን ህብረተሰብ ያለአድልኦ፣ በአክብሮትና በታማኝነት ማገልገል፣ እንዲሁም ሁሌም መማርና መሻሻል እንደሚያስፈልግ ዶ/ር አሚር አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የጤና ተቋማት ባለሙያዎችን አቅም በየጊዜው በማሳደግና ከወቅቱ ጋር ከማዘመን፣ የእናቶችና ህጻናት ሞት መጠን ከመቀነስ፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋንን ከማሻሻል፣ ተላላፊ በሽታዎችን  ከመቆጣጠርና ከመከላከል እንዲሁም የወባ በሽታ ስርጭትን ከመግታት አኳያ የዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ አበረታች ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ ገልጸዋል፡፡ ግዙፉ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ተጠናቆ ሥራ ሲጀምርም የጤና ትምህርት ጥራትን ይበልጥ የሚያሳድግ እንዲሁም ጥራት ያለውና ተደራሽ የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ተመራቂዎች በሰጡት አሰተያየት የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት በገቡት ቃለ መሃላ መሠረት ወደ ተግባር በመለወጥ ህብረተሰቡን በፍቅር፣ በርህራሄና በሙያዊ ሥነ-ምግባር ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አሚር አማን፣ የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳ ክብርት አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡