ከ35 ሚሊዬን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአርክቴክቸር ዲዛይን ስቱዲዮ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ በ1600 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ስቱዲዮ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን የኮምፒዩተር ላቦራቶሪ፣ የዲዛይን ስቱዲዮ፣ ሙዝዬምና የመማሪያ ክፍሎች ይገኙበታል፡፡

የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ግዛው ፍቅሬ እንደገለፁት ትምህርት ክፍሉ በ1997 ዓ/ም ሲከፈት በቂ የሰው ኃይል፣ ግብዓትና የመማሪያ ስቱዲዮ ያልነበረው በመሆኑ ቅሬታዎች ይስተዋሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ትምህርት ክፍሉ የግብዓት ክፍተቶች ቢኖሩትም በሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን የተማሪዎች ዲዛይን ውድድሮች በመሳተፍ በ2007 ዓ/ም የሁለተኛነት እንዲሁም በ2008 ዓ/ም ከ17 ዕጩዎች የአንደኛነት ደረጃ ሊያገኝ ችሏል፡፡ በመሆኑም የስቱዲዮው መገንባት ትምህርት ክፍሉ ከዚህ ቀደም የነበሩበትን ችግሮች በመቅረፍ ብቃትና ክህሎት ያላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምሁራንን ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ መምህር አቶ ሃጎስ አማን ስቱዲዮው የተማሪዎችን የትምህርት ተነሳሽነት ከማሳደጉም በተጨማሪ ጥሩ የፈጠራ ክህሎት የታከለባቸው የዲዛይን ሥራዎችን እንዲሠሩ የጎላ ፋይዳ  አለው፡፡

የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ትምህርት ክፍል የ6ኛ ዓመት ተማሪ መሳፍንት ወይብ ትምህርት ክፍሉ ቀደም ሲል የተሟላ ስቱዲዮ የሌለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ ገልፆ የስቱዲዮው መገንባት ለተማሪዎች መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ተናግሯል፡፡

በትምህርት ክፍሉ ከ1ኛ ዓመት እስከ 6ኛ ዓመት በ15 ሴክሽን  240 ወንድና 80 ሴት በድምሩ 520 ተማሪዎች እንዲሁም 21 የሀገር ውስጥና 7 የውጭ  ሀገር መምህራን ይገኛሉ፡፡