‹‹ሽልማቱ በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚመጡ ተማሪዎች ትልቅ ማነሳሻ ነው››አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴ

ዩኒቨርሲቲው ከየትምህርት ክፍሉ የላቀ ውጤት ላመጡ ሴት ተማሪዎች ኅዳር 16/2009 ዓ/ም የማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷል፡፡

የፕሮግራሙ ዓላማ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለተቀላቀሉ አዲስ ሴት ተማሪዎች በራስ መተማመንን መፍጠርና ተሸላሚ ተማሪዎች  በቀጣይ የትምህርት ዘመን ከቀድሞ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ  ማበረታታት እንደሆነ የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

በዩኒቨርሲቲው የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት በመሠራቱ ጉልህ ለውጥ መታየቱንና ተሳትፎውም ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት በ2009 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው በመደበኛ ቅድመ ምረቃ የሴት ተማሪዎች ቁጥር 43% የደረሰ ሲሆን በሁሉም የትምህርት መስኮች በማዕረግና በከፍተኛ ማዕረግ የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡

ሴቶችን ማብቃት ማህበረሰቡን ለማብቃት ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑ ታምኖበት በብሔራዊ ደረጃ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሌሎችም ዘርፎች ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ እስከሚሆኑ ድረስ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሴቶችን የማብቃትና በተለያዩ መዋቅሮች ወደ አመራር የማምጣት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአካ/ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ገልፀዋል፡፡ ተሸላሚ ተማሪዎች መልካም አርአያነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና ሌሎች ሴት ጓደኞቻቸውን በማበረታታት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም አሳስበዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴ የህይወት ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች ያካፈሉ ሲሆን ሽልማቱ በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚመጡ ተማሪዎች ትልቅ ማነሳሻ ነው ብለዋል፡፡ ሴትነት ከውጤታማነት እንደማያግድ፣ ችግሮችን ተቋቁሞ በማለፍ ለዓላማ መትጋት እንደሚገባና ህይወታቸውን ስኬታማ ለማድረግ ሁሌም የተሻለ ሆነው መገኘት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

ሽልማቱ ተማሪዎች በቀጣይ የበለጠ ሠርተው ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ የሚያበረታታና ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን ተሸላሚ ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አስተማሪ የሆነ የህይወት ተሞክሮ ያላቸውን ሴት ምሁራን ጋብዞ ልምድ እንዲያገኙ መደረጉ ይበል የሚያሰኝና ጥንካሬን የሚፈጥር ሲሆን በተሰለፉበት መስክ ማንኛውንም ችግር ለማለፍ የሚያስችል ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴ፣ የቀድሞዋ የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሙኒት መኩሪያ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡