ሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት የጤና አጠባበቅ ጣቢያዎችንና ት/ቤቶችን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ዩኒቨርሲቲው ከሳሃይ ሶላር አሶሲዬሽን አፍሪካ እና ከጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር ጋር በሳሃይ ሶላር የ3 ዓመት አፈፃፀም ላይ ለመወያየትና ቀሪ 35 ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የጋራ ሥራዎችን ለማጠናከር ጥር 24/2009 ዓ.ም ምክክር አድርጓል፡፡

በገጠሩ አካባቢ የሚታየውን የኤሌክትሪክ ኃይል እጦት መቅረፍና የአካባቢውን ወጣቶች በዘርፉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግን ዓላማ አድርጎ ፕሮጀክቱ መቋቋሙን የፕሮጀክቱ ሊቀመንበርና የዩኒቨርሲቲው የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ግርማ ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በሚያዝያ/2015 ሥራውን ሲጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ በዞኑ 8 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችንና 15 የጤና አጠባበቅ ጣቢያዎችን የ24 ሰዓት የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን የተቀሩት 35 ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች በተያዘላቸው ጊዜ መሠረት ዕድሉን እንደሚያገኙ አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡ ከፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ በጀት 6,900,000 ብር በሳሃይ ሶላር፣ 1,700,000 ብር በጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር እና 1,640,000 ብር በዩኒቨርሲቲው የሚሸፈን ይሆናል፡፡

አቶ ዘላለም አክለውም ቴክኖሎጂውን ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግና ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ በርካታ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ት/ቤቶችና የጤና ተቋማት የሬድዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፒዩተር፣ ማባዣ ማሽኖች፣ ላቦራቶሪ፣ ማቀዝቀዣና የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የግንዛቤ አለመኖር፣ የቁሳቁስ አቅርቦት ማነስ፣ የመለዋወጫ ባትሪዎች እጥረትና የርዕሳነ መምህራን በየጊዜው መለዋወጥ ሊቀረፉ የሚገባቸው ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ዓላማ መሳካት ዞኑ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ወረዳዎችና ቀበሌያት ድረስ ወርዶ በጋራ ለመሥራትና ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረው አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ለማድረግ መዘጋጀቱን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ ተናግረዋል፡፡

በጀርመን የፕሮጀክቱ ሊቀመንበር ሚስተር ማክስ ፓውል በበኩላቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመሥራታቸው የታየው ስኬት ያስደሰታቸው መሆኑን ገልፀው በዩኒቨርሲቲው ባለ 5 ኪሎ ዋት ሶላር ሲስተም ተከላ እንደሚያደርጉና ለነባር የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተማሪዎችና ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞኑ አመራሮች፣ የፕሮጀክቱ አጋር ሀገራት ከሆኑት ጀርመንና ስዊዘርላንድ የመጡ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡