የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ አስፈፃሚዎች፣ ከ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ርዕሳነ መምህራንና የሥልጠና ቦርድ አባላት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ወላጆቻቸውን በኤች አይ ቪ/ኤድስ ላጡ ተማሪዎች ሊደረግላቸው ስለሚገባ ድጋፍና እንክብካቤ ጥር 4/2009 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ኤች አይ ቪ/ኤድስ በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን በርካታ ህፃናትን ወላጅ አጥ ያደረገ መሆኑን የተናገሩት የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ዓለሙ የውይይቱ ዓላማ በትምህርት ቤትና ከት/ቤት ውጭ ያሉ ወላጅ አጥ ህፃናት ተማሪዎችን በመንከባከብና በመደገፍ ከኤች አይ ቪ/ኤድስ የፀዳ ትውልድን ለመፍጠር የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው ብለዋል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለጹት ተማሪዎች በኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ከሚያስችሉ መንገዶች ጥቂቶቹ የህይወት ክህሎት ሥልጠና፣ የእርስ በእርስ ውይይት እና የሥነ-ተዋልዶ ጤናና ኤች አይ ቪ/ኤድስ ክበብን ማቋቋምና ማጠናከር ናቸው፡፡ ጎዳና ተዳዳሪ፣ አካል ጉዳተኛ፣ ተጥለው የተገኙ፣ ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸው እና ለወሲብ ጥቃት የተጋለጡ ህፃናት ድጋፍ ሊደረግላቸው ከሚገባቸው ህፃናት መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ህፃናት የጀመሩትን ትምህርት ሳያቋርጡ ጤንነታቸው ተጠብቆ መልካም ትውልድ መገንባት እንዲቻል ዩኒቨርሲቲው ተጋላጭና ወላጅ አጥ ህፃናትን የችግር ዓይነታቸውን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ በዘላቂነት እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ ተማሪዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ዩኒቨርሲቲው በሥርዓተ ትምህርት አካቶ በ3 ክሬዲት ሃወር ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና በቫይረሱ ወላጆቻቸውን ያጡና ተጋላጭ ህፃናትን በመደገፍ ረገድ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ መሥራቱ መልካም ጅምር መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን ሥራውን ዳር ለማድረስም ቃል ገብተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለ60 የአርባ ምንጭ ከተማና የዙሪያ ወረዳዎች ወላጅ አጥ ተማሪዎች የዩኒፎርም ጨርቅ፣ የማሰፊያ ገንዘብና የቦርሳ ድጋፍ አድርጓል፡፡