121ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዩኒቨርሲቲው ተከበረ

የማኅበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ከታሪክና ቅርስ አስተዳደር ት/ክፍል ጋር በመተባበር 121ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የካቲት 23/2009 ዓ.ም በሲምፖዚየም አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

በሲምፖዚየሙ የአድዋ ጦርነት ታሪካዊ ዳራዎችና ድሉን የሚዘክሩ የተለያዩ ጽሑፎች በትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ካሱ ጡሚሶ፣ መምህር ተስፋዬ አክሊሉ፣ መምህር መሀመድ ሰይድ እና ሌሎች ምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም አድዋን ሲገልፁ ‹‹በጊዜ፣ በሥፍራና በተዋናዮች የተከናወነ እና የሚጠና፣ የሚመረመር፣ የሚፃፍ ታሪክ፤ በህዝብ ህሊና ህያውነት ያገኘ ትውስታ፤ በታሪካዊትና ዘመናዊት ኢትዮጵያ የታሪክ ድልድይ፤ በግፉአን ህዝቦች ዘንድ የነፃነት፣ የማኅበራዊ ፍትህና የተስፋ ተምሳሌት ነው›› ብለዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ካሱ ጡሚሶ ‹‹The Victory of Adwa: it’s Inspiration & our Legacy›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ የአድዋ ድል አሻራና ተሞክሮ፣ ከአድዋ አስቀድሞ የነበሩ ጦርነቶች፣ ለአድዋ ጦርነት ምክንያት የነበሩ መሠረታዊ ነገሮች፣ የጦርነቱ ሂደትና የኢትዮጵያ ድል እንዲሁም በአድዋ ጦርነት የሴቶችን ሚና ዳሰዋል፡፡ እንደ አቶ ካሱ ገለፃ የአድዋ ድል ጥቁሮች ከባርነት እንዲወጡ መንገድ የጠረገ የመጀመሪያው የጥቁሮች ነፃነት ፋና ወጊ ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች አንድነት ፈጥረው ስለ መብትና ነፃነታቸው መጠየቅ የጀመሩትም ከአድዋ ድል ማግስት ነው፡፡ በመሆኑም አድዋ ታላቅ ድል መሆኑ በኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጥቁሮችና አውሮፓውያን ዘንድም ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ ነበር፡፡

አባት አርበኛ ባሻ መንገሻ መኩሪያ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ጀግኖች አባቶቻችን አድዋ ላይ በሠሩት ተጋድሎ የወራሪ ፋሽስቶችን ዕብሪት መክተው ነፃነቷን የጠበቀች ሀገር ያስረከቡን በመሆኑ ወጣቱ ትውልድም የሀገሩን ታሪክ ጠንቅቆ ማወቅና የአባቶችን አሻራ ማስቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ሁሉም የሰው ዘር እኩል እንደሆነ በኩራት ያሳዩበት፣  ጀግንነታቸውንና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከሩበት እንዲሁም ኢትዮጵያን በዓለም ዓቀፍ መድረክ ያስከበረ ትልቅና ሲዘከር የሚኖር ድል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጀግኖች አባቶቻችን ያሳዩትን አንድነትና ቆራጥነት የሚጠይቅ ዋነኛ ጠላታችን ድህነት በመሆኑ ከቀደምት ጀግኖቻችን በወረስነው ወኔና መንፈስ በድህነት ላይ መዝመት ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የዕለቱ የክብር እንግዳ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ት/ክፍል መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም አባትና እናት አርበኞች በዓሉን ታድመዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት