ዩኒቨርሲቲው 41ኛውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓል በድምቀት አከበረ

በሀገራችን ለ41ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓልን ‹‹የሴቶችን አቅም በትምህርትና ስልጠና በመገንባት በአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ያላቸውን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንተጋለን!›› እና ‹‹የሴቶች የቁጠባ ባህል ማደግ የህዳሴያችን  መሰረት ነው፡፡›› በሚሉ መሪ ቃሎች ዩኒቨርሲቲው መጋቢት 14/2009 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የስርዓተ - ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ እንደገለፁት የበዓሉ ዓላማ የዓለም መንግስታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል ፖሊሲዎቻቸውን፣ ህጎቻቸውንና አሰራሮቻቸውን በመፈተሽ ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ መድሎዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ማነሳሳት ነው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ሴቶች የሚደርስባቸውን ጭቆናና የመብት ጥሰት የሚያወግዙበት፤ አንድነታቸውን በማጠናከር ድምፃቸውን በጋራ የሚያሰሙበት እንዲሁም ልምድ የሚለዋወጡበትና ለበለጠ ትግል ተቀናጅተው ለመንቀሳቀስ ቃል የሚገቡበት ቀን ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሯ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ሴቶች ያለባቸውን ድርብ ጫና ከግንዛቤ በማስገባትና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በሁሉም መስክ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚሠራ መሆኑን ገልፀው ሴቶች ልምድ በመለዋወጥ፣ ምርምሮችን በመሥራት፣ በአመራር ቦታዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም የቁጠባ ባህላችንን በማሳደግ ለሀገራችን እድገት የበኩላችንን አሻራ መጣል ይገባናል ብለዋል፡፡ በተለይም ሴት መምህራን ተማሪዎችን ለማብቃትና በሴትነታቸው ከሚደርሱባቸው ተፅዕኖዎች ለመከላከል ኃላፊነት ተሰምቷቸው እንዲሰሩም  አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት በዓሉ ሲከበር የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥና ሴቶች በልማት ሥራ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ በቁርጠኝነት በመነሳት ነው፡፡ በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮ አንፃር ዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎች በዕውቀትና በክህሎት ተክነው በመመረቅ በሀገሪቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ባለሙያነትና ኃላፊነት ቦታዎች የሚሠሩ ዜጎች እንዲሆኑ እና ሴት ሠራተኞችን ወደ አመራርነት ቦታ ለማምጣት ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና የሚያመላክት የስዕል አውደ ርዕይ፣ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች እንዲሁም የሴቶች ቴኳንዶ፣ ገመድ ጉተታና የዱላ ቅብብል ውድድሮች የበዓሉ አካል ሲሆኑ በያዝነው የትምህርት ዘመን በ1ኛ መንፈቀ ዓመት የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች፣ የተሻለ የማጠናከሪያ ትምህርት ለሰጡ የትምህርት ክፍሎችና ኮሌጆች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡