አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ያሠለጠናቸውን 74 ወንድና  21 ሴት በድምሩ 95 ተማሪዎች ለ6 ጊዜ ሐምሌ 14/2015 ዓ/ም አስመርቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የጎፋ ዞን አስተዳዳሪና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው የለውጥ መሠረት የሆነውን ትምህርት በማስፋፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ድርሻ ያለው ተቋም መሆኑን ጠቅሰው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው የመውጫ ፈተና የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት ባሻገር መንግሥት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ለመስጠቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ጌትነት ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የገበዩትን ዕውቀትና ክሂሎት ለሀገር ልማት ለማዋል ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ፣ ማኅበረሰባቸውን በትጋት እንዲያገለግሉ እና የሀገር አንድነትን ለመገንባት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለስኬታቸው የማይተካ ዋጋ ለከፈሉ ወላጆቻቸው፣ መምህራንና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የጥረታቸውን መልካም ፍሬ እንዲያሳየቸውም አደራ ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ሳውላ ካምፓስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ከጀመረ ጀምሮ ባሉት ስምንት ዓመታት ከመማር ማስተማር ባሻገር በምርምርና የማኀበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች የራሱን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ተናግረዋል። በዚህም በካምፓሱ በ2015 በጀት ዓመት 57 መምህራን በምርምር ሥራ የተሳተፉ ሲሆን 13 ምርምሮች መጠናቀቃቸውንና ሁለቱ ወደ ፕሮጀክት ተቀይረው ወደ ማኀበረሰቡ መውረድ መቻላቸውን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

ካምፓሱ በምሥረታ ዕድሜው አጭር ጊዜያትን ያስቆጠረና ከዋናው ግቢ ራቅ ብሎ የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር መሠረተ ልማት ለማሟላትና ለሁለንተናዊ እድገቱ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን ይጠይቃል ያሉት ፕሬዝደንቱ ካምፓሱ በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ እንዲሆን የአካባቢው ማኀበረሰብ ድጋፍ እንዳይለየው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገብረመድኅን ጫሜኖ እንደተናገሩት ካምፓሱ በ2015 የትምህርት ዘመን በ30 የትምህርት ፕሮግራሞች 3,199 ተማሪዎችን ሲያስተምር የቆየ ሲሆን የዘንድሮ ተመራቂዎችን ጨምሮ ካምፓሱ በስድስት ዙሮች 1,620 ተማሪዎችን ለምረቃ አብቅቷል፡፡

ካምፓሱ በተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ማስመረቁን ያስታወሱት ኃላፊው በዘንድሮው ዓመትም 3.97 የመመረቂያ ነጥብ ያላቸው ተማሪዎችን በማፍራቱ የውጤቱ ባለቤቶች ለሆኑ ተማሪዎች፣ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መምህራንና ለመላው የካምፓሱ ማኅበረሰብ ደስታቸውን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በሀገሪቱ የተለያዩ ቁልፍ ቦታዎች በሙያቸው እያገለገሉ መሆኑ እንደሚያኮራቸው የተናገሩት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ኅብረት (አልሙናይ) ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ የዘንድሮ ምሩቃንም የኅብረቱ አባል ሆነው በምርምር፣ ሥልጠና፣ ዩኒቨርሲ- ኢንደስትሪ ትስስር፣ ማኅበረሰብ አገልግሎትና ሌሎችም የተለያዩ መስኮች ዩኒቨርሲቲያቸውን መልሰው እንዲያገለግሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ከካምፓሱ አጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 3.9733 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ተክለማርያም ተስፋዬ የወርቅ ሜዳሊያ የተሸለመ ሲሆን ከሴት ተማሪዎች መካከል 3.89 ያስመዘገበችው ተማሪ ገነት መኮንን ልዩ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ 3.97 በማምጣት በጥቂት ነጥቦች ልዩነት የወርቅ ሜዳሊያውን ላላገኘው ተማሪ ረቢራ ኡርጌ የጎፋ አካባቢ ተራድዖ ማኅበር 10,000.00 ብር የማበረታቻ ሽልማት አበርክቶለታል፡፡

የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመለከተው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2015 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ከወሰዱ 3,147 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች 2,366ቱ ወይም 75.18 በመቶው የማለፊያ ውጤት አግኝተዋል፡፡ የመውጫ ፈተናውን ከወሰዱት መካከል 374ቱ የሳውላ ካምፓስ ተማሪዎች ሲሆኑ 272 ተማሪዎች ወይም 72.72 በመቶ ፈተናውን አልፈዋል ብለዋል፡፡

የጎፋ ልማት ማኅበር በምረቃቸው ላይ ቤተሰቦቻቸው ላልተገኙላቸው ሁለት ተመራቂዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለሻ ትራንስፖርትና ተያያዥ ወጪዎችን እንዲሸፍንላቸው ለእያንዳንዳቸው የ6,000.00 ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት