የኮሚኒቲ ት/ቤቶች የተማሪ ወላጆች ጉባኤ ጥቅምት 18/2010 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ የተማሪዎች ሥነ-ምግባር፣ ወላጆች በት/ቤቱ ውስጥ ያላቸው ሚና፣ የት/ቤቶቹ የ2010 1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም እንዲሁም ወላጅ መምህር ህብረት ማስመረጥ የጉባኤው መወያያ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የጉባዔው ዋና ዓላማ የመንግሥት፣ የዩኒቨርሲቲው እንዲሁም የማህበረሰቡ ትኩረት የሆነውን የትምህርት ጥራት በ2010 የትምህርት ዘመን በኮሚኒቲ ት/ቤቶች ማምጣት እንዲሁም ተማሪዎቹን በመልካም ሥነ-ምግባር ማነጽ በሚቻልበት ሁኔታ ግንዛቤን መፍጠር መሆኑን የማህረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ገልፀዋል፡፡

‹‹የትምህርት ሥርዓት በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የታገዘ ካልሆነ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ  የሚታሰብ አይደለም፡፡›› ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለሀገሩና ለቤተሰቡ የሚጠቅም ልማታዊ አስተሳሰብን ያነገበ ዜጋ እንዲፈጠር የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው እንደተገለፀው ዩኒቨርሲቲው ከኮሚኒቲ ት/ቤት በተጨማሪ የአርባ ምንጭ እና የሣውላ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤቶችን በቴክኖሎጂ በማገዝ የተሻሉ ተማሪዎች እንዲያፈሩና ለሌሎች ት/ቤቶች ሞዴል የልህቀት ማዕከላት እንዲሆኑ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኮሚኒቲ ት/ቤት በ2009 የትምህርት ዘመን ካስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል 128 የተፈጥሮና ማህበራዊ ሣይንስ ተማሪዎች 127ቱ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ሲሆን የ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና የወሰዱ 88 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ የመሰናዶ ትምህርት መግቢያ ውጤት አምጥተዋል፡፡

የኮሚኒቲ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤት ር/መር አቶ ካምቦ ከተማ የ2010 ትምህርት ዘመን 1ኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት የተማሪዎቹ ውጤት አበረታች ቢሆንም በሥነ-ምግባር በኩል ሰፊ ክፍተቶች በመኖራቸው ከውጤቱ ጎን ለጎን ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ወላጆች ከዩኒቨርሲቲው ጎን ሊቆሙ ይገባል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ተማሪዎቹ ያስመዘገቡት ውጤት በራሳቸው በተማሪዎች፣ በዩኒቨርሲቲው፣ በመምህራንና በትም/ርት ቤቱ አመራሮች የተገኘ መሆኑን አውስተው በቀጣይም በጥሩ ሥነ-ምግባር ታንጸው ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡