የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ከኢትዮጵያ አካውንቲንግና ኦዲቲንግ ቦርድ ጋር  በመሆን ለአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል 30 መምህራን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃ /IFRS/ ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና ከጥር 7/2010 ዓ/ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ልሳነወርቅ አማረ በስራ ላይ ያሉት የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች በመቀየራቸው መምህራን በአዲሱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃ መሰረት በዕውቀትና በክህሎት ብቁ ሆነው ተማሪዎቻቸውን እንዲያስተምሩና ለሌሎችም መረጃውን ተደራሽ በማድረግ የሀገሪቱ የሪፖርት አቀራረብ ዘዴ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል የስልጠናው ዓላማ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ዓመትም የቀድሞው የአካውንቲንግና ፋይናንስ ሥርዓተ-ትምህርት ተቀይሮ በአዲሱ ደረጃ መሰረት ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካውንቲንግና ኦዲቲንግ ቦርድ የኦዲት ጥራት ሲኒየር ማኔጀር አቶ ታምራት እሸቱ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን/ IFRS/ በአዋጅ ቁጥር 847/2006 ዓ/ም የተቀበለች ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 332/2008 ዓ/ም የኢትዮጵያ አካውንቲንግ ቦርድ ተቋቁሟል፡፡ ቦርዱ ሪፖርት አቅራቢ ድርጅቶችን አቅም የመገንባትና የመቆጣጠር ስልጣን ስለተሰጠው  በአሁኑ ሰዓት  አፈፃፀሙን እየተከታተለ መሆኑን አቶ ታምራት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ዘሩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በመወያያ ሰነዱ የIFRS ምንነት፣ አስፈላጊነትና ተጠቃሚዎቹ የሚሉ አንኳር ሀሳቦች ተካተውበታል፡፡

አቶ ፈጠነ እንደገለፁት በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ወጥ የሆነ የሪፖርት አሰራር ያልነበረ ሲሆን የሪፖርት አቀራረብ ደረጃውም ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ለግብር እንዲያመች ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ ለሌላ አካል መቅረብ የሚችል አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሪፖርት አቅራቢ አካላት በአዲሶቹ ደረጃዎች መሰረት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ደረጃዎቹን መቀበሉን ተናግረዋል፡፡ የሚቀርበው ሪፖርት ማንኛውም ዜጋ ሊረዳው የሚችለውና  ከሌሎች የውጪ ሀገራት የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ፈጠነ ገለፃ ደረጃዎቹን ተከትሎ የሚሰራ ማንኛውም የሂሳብ ሪፖርት እውነትን መሰረት ያደረገና የህብረተሰቡን ጥቅም የሚያስከብር እንዲሁም መንግስት የሚገባውን ግብር እንዲሰበስብ አመቺ ነው፡፡ በተጨማሪም ጥራት ያለው ሪፖርት የውጪ ባለሀብቶች ወደ ሀገራችን እንዲመጡ የተመቻቸ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ከመሆኑም ባሻገር በቀላሉ ብድር ለመበደርና ለማበደር እንዲቻል ይጠቅማል ብለዋል፡፡

የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የኦዲት ማረጋገጥ ደረጃዎች ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ መለሰ በበኩላቸው አንድ ሪፖርት አቅራቢ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን ከደረጃ 1-17 በቦርዱ የተቀመጡ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች /IFRS/ እና ከዚህ በፊት የነበሩት ኮሚቴዎች ያወጧቸውን ከ1-41 ያሉ ዓለም አቀፍ የአካውንቲንግ ደረጃዎች/IAS/ ተቀብሎ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በባለሙያዎቹ ምላሽ የተሰጣቸው ሲሆን በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ቀጣይ ስራዎች ላይ አስተያየትና ጥቆማዎች ተደርገዋል፡፡ በIFRS የተቃኘ ሥርዓተ-ትምህርት ማዘጋጀት፣ ፕሮጀክት በመንደፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግ፣ ከኢትዮጵያ አካውንቲንግ እና ኦዲቲንግ ቦርድ ጋር በመተባበር በስታንዳርዱ ተግባራዊ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር መፍታት እንዲሁም ለአካባቢው፣ ለዞኑና ለክልሉ የቢዝነስ ማህበረሰብ ስልጠና፣ ድጋፍና የማማከር አገልግሎት መስጠት ከት/ክፍሉ ቀጣይ ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የት/ክፍሉ ኃላፊ አቶ ልሳነወርቅ አማረ ገልፀዋል፡፡

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ በመዝጊያ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ እና የጥናትና ምርምር ቦታ እንደመሆኑ መጠን በንድፈ ሀሣብ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን ያሉንን ውስን ሀብቶች በአግባቡ አሟጠን እንድንጠቀም የሚያግዙ መሰል የጥናትና ምርምር ውጤቶች የሚፈተሹበትና ወደ ተፈፃሚነት እንዲሸጋገሩ ድልድይ በመሆን የሚያገለግል ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው ከየትኛውም የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ቀደም ብሎ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መጀመሩ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንድንሰራበት የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ስልጠናው መምህራንን በማሰልጠን ብቻ የሚቋጭ ሳይሆን ተማሪዎች፣ የአካባቢውን የንግድ ማህበረሰብና በዘርፉ በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ሀገሪቱ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር አንድ ዓይነት የሪፖርት ቋንቋ እንዲኖራትና እድገቷን እንድታፋጥን ዩኒቨርሲቲው በንቃት የሚሰራ መሆኑን ዶ/ር መልካሙ ገልፀዋል፡፡

ሰልጣኝ መምህራን በሰጡት አስተያየት አዲሱን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀው በቀጣይ ያገኙትን ዕውቀት ለተማሪዎቻቸውና ለንግዱ ማህበረሰብ ተደራሽ እንደሚያደርጉና የተለያዩ የምርምር ተግባራትን ለማከናወን  የሚጠቅማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናውን የተከታተሉ መምህራን ከኢትዮጵያ አካውንቲንግና ኦዲቲንግ ቦርድ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡