አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡ የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱም በዩኒቨርሲቲው ፌስቡክ ገጽ እና ዩቲዩብ ቻናል በቀጥታ ተላልፏል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በ6 የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው፡፡ በመሆኑም የዛሬ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል፡፡ ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ም/አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት