አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ‹‹ጥራት ያለው ትርጉምና ተርጓሚነት ለሀገራዊ መግባባት!›› በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 24-25/2013 ዓ/ም የመጀመሪያውን ሀገራዊ የትርጉም እና የተርጓሚነት ጉባዔ በዩኒቨርሲቲው አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቋንቋና ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ ኢንስቲትዩቱ ከተመሠረተ አንድ ዓመት ያልሞላው ቢሆንም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ጉባዔ ማዘጋጀቱ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ከከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመሥራት የሦስትዮሽ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን በቀጣይም በሥዕል፣ በሙዚቃና በሥነ-ጥበብ ፍላጎት ያላቸውን መምህራንና ተመራማሪዎች ከአካባቢው ማኅበረሰብ በመመልመልና በማሠልጠን የአካባቢውን ቱባ ባህልና ዩኒቨርሲቲውን ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ የሚሠራ መሆኑን ዶ/ር ሰኢድ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ለዜጎች መቀራረብና ሀገርን በጋራ ለመገንባት፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅና በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ ትርጉም ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለሀገራችን ከማንኛውም ጊዜ በላይ የትርጉም ሙያተኞች ያስፈልጓታል ያሉት ዶ/ር ሂሩት ተጨባጭ ሥራ ለመሥራት በጋራ መቆም የሚገባ መሆኑን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና ትርጉም ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አውላቸው ሹምነካ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ፣ የእምቅና ድንቅ ባህላዊ እሴቶችና ከ80 በላይ ቋንቋዎች ባለቤት መሆኗን አውስተው ኢትዮጵያ ካሏት ቋንቋዎች 53ቱ የትምህርት ቋንቋ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ቋንቋዎች የዚህ ዕድል ተቋዳሽ መሆን አልቻሉም ብለዋል፡፡ ቋንቋዎች የያዟቸውን የተለያዩ ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ እሴቶችና አስተሳሰቦች ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ ትርጉምና የተርጓሚነት ሙያ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ዶ/ር አውላቸው ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተልዕኮውን ለመወጣት እንዲያስችለው ካቋቋማቸው የምርምር ልኅቀት ማዕከላት አንዱ የባህልና ቋንቋ ልኅቀት ማዕከል ሲሆን በማዕከሉ ከባህልና ቋንቋ አንፃር የሚያስፈልጉ የምርምርና ሥልጠና ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ዘርፉን በትምህርት አስደግፎ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር የሚያከብሩ፣ በታማኝነት በሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ዜጎችን ለማሠልጠንና የትርጉምና የተርጓሚነት ሙያ ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲው ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የበኩሉን ድርሻ በትጋት እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው 13 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ‹‹የትርጉም ታሪካዊ ዳራ፣ የትርጉም ዐውድ፣ ተርጓሚና ትርጁማን በኢትዮጵያ››፣ ‹‹በትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ እና ተግባር ዙሪያ ሀገራዊ የዳሰሳ ጥናት››፣ ‹‹የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚነት በኢትዮጵያ አጠቃላይ ገጽታ››፣ ‹‹Translation as a Tool for National Consensus፡ A Lesson from Turkey›› እና Amharic-English Machine Translation ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአርባ ምንጭ የኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ት/ክፍል መምህርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ዘመኑ ሐዲስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከ4 ሺህ ዓመት በላይ የዘለቀ የትርጉም ሥራና የትርጁማንነት ታሪከ እንዳላት ጠቅሰዋል፡፡ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ክርስትና እንዲሁም በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ እምነቶቹን ለማስፋፋት፣ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡና የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ምዕመናንን ለማግባባትና የባህል ውርርስ ለማካሄድ የትርጁማኖች ሚና ከፍተኛ እንደነበር በጥናታዊ ጽሑፉ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግሥት ዓለማየሁ ከጉባዔው በርካታ ቁምነገሮችን መቅሰማቸውን ተናግረው በተለይ ‹‹መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በምልክት ቋንቋ ተርጓሚነት›› በሚል ርዕስ የቀረበው ገለጻ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በተለያዩ ተቋማት በተርጓሚ እጦት በእጅጉ ይቸገራሉ ያሉት ሥራ አስኪያጇ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምልክት ቋንቋ ተርጓሚነት ትምህርት ሊጀምር መሆኑ ለችግሩ መፍትሄ አንድ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት