የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃ አቅርቦትና ሳኒተሪ ምኅንድስና የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራም ለማስጀመር ሚያዝያ 2/2013 ዓ/ም የሥርዓተ ትምህርት የውስጥ ግምገማ አካሂዷል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ እንደመለየቱ በ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት 5 ዓመታት 5,000 የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ለማስመረቅ ያቀደ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ፕሮግራሙን መክፈቱ ለዚህ ሀገራዊ ዕቅድ መሳካት የበኩሉን አስተዋፅኦ የሚያበረክትበት ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል በበኩላቸው ሥርዓተ ትምህርቱ የሀገሪቱን ችግር ያማከለ መሆኑን ለማረጋገጥ ግምገማው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው በቅርቡ ሥርዓተ ትምህርቱ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ሲጸድቅ ተማሪዎችን መቀበል እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ደመላሽ ወንድማገኘሁ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በቀጣይ የውጭ ግምገማ በማስደረግ ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊውን ግብዓት አሟልቶ ፕሮግራሙን በቅርቡ ለመክፈት በሚያስችለው ሁኔታ ላይ ነው ብለዋል፡፡

የውሃ አቅርቦትና ሳኒተሪ ምኅንድስና መምህር ዶ/ር ታምሩ ተሰማ እንደገለጹት ሀገር በቀል ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እንዲቻልና የውሃ ሀብቱን በአግባቡ ለመጠቀም በተመረጡ ፕሮግራሞች የሠለጠነ የሰው ኃይል ቢያስፈልግም በ3ኛ ዲግሪ ላይ የምሁራን ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውሃ አቅርቦትና ሳንተሪ ምኅንድስና፣ በከርሰ ምድር ውሃ እና በመስኖ የ3ኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሉት መሆኑን ዶ/ር ታምሩ ተናግረዋል፡፡

በሥርዓተ ትምህርት ግምገማው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር፣ ሥርዓተ ትምህርቱን ያዘጋጁ እና ሌሎችም መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት