የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የሶሾሎጂ እና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ቤልጂየም፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞዛምቢክ፣ ዝምባብዌ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍሎች ጋር በመተባበር ከሚያዝያ 4 - 13/2013 ዓ/ም ድረስ ለተከታታይ 10 ቀናት የመስክ ትምህርት /Field School/ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ሳህለ ሰይድ እንደገለጹት የፕሮግራሙ ዓላማ በ5ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የሶሾሎጂ ወይም የካልቸራል አንትሮፖሎጂ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በተመረጡ ርዕሶች ላይ ምርምር እንዴት እንደሚሠራ እንዲሁም በአንድ ንዑስ ሃሳብ ላይ ሰፊና ጥልቀት ያለው ተግባራዊ እውቀትና ልምድ የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸትና መሠረታዊ የእውቀት ሽግግርን ማካሄድ ነው ብለዋል፡፡

መ/ር ሳህለ አክለውም የፕሮግራሙን አጀማመር አስመልክተው እንደተናገሩት በቤልጂየም ዓለም አቀፍ እርዳታ /VLIRUOS/ አማካኝነት የ5ቱ ባለድርሻ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ክፍሎች ለየብቻቸው የሚፈራረሙበት ሆኖ እንደተጀመረም ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ በዋነኛነት መሠረት ያደረገው የባለድርሻ ዩኒቨርሲቲዎቹ መምህራንን አቅም ማጎልበትና በምርምርና በንድፈ ሃሳብ እውቀትን መለዋወጥ ላይ ነውም ብለዋል፡፡ ይህም ከኮቪድና ሌሎች ከጤና ጋር የተገናኙ ችግሮችን ግምት ውስጥ ያስገቡ የአንትሮፖሎጂ ምርምሮች እንዲወጡ የሚረዳ መሆኑን መ/ር ሳህለ ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ የተካሄደው በኦንላይን ሲሆን በቆይታውም ከባለድርሻ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ፕሮፌሰሮችና መምህራን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግር የሆነው ኮሮና ቫይረስ በማኅበረሰቡ ላይ እያሳደረ በሚገኘው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች ዙሪያ ለ5ት ቀናት ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድ አጫጭር ጥናቶችን ያካሄዱ ሲሆን ያገኟቸውን ግኝቶች ሁሉም አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተሳታፊ መምህራን በሰጡት አስተያየት በመስክ ትምህርት ፕሮግራም ላይ በመሳተፋቸው ሰፊ እውቀት፣ ግንዛቤና ልምዶችን እንዲያገኙ ያገዛቸው መሆኑንና በተለይ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ወረርሽኞች ሲነሱ የአንትሮፖሎጂ ባለሙያዎች ማድረግ ባለባቸው አስተዋጽኦ ዙሪያ ጠቃሚ ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ በተጨማሪም የተለያዩ የአንትሮፖሎጂ ምርምር ዘዴዎች እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረጉና ከኮሮና ቫይረስ ራስን በመከላከልና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መሰል ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እንደሚቻል የተሻለ ልምድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ የሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህራንና የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲሁም ከማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የተወጣጡ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት