የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት 7ኛውን ሀገር አቀፍ ምርምር ለልማት ጉባዔ ከሚያዝያ 29-30/ 2013 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የምርምር ጽሑፎች በመሰል አውደ ጥናቶች እየቀረቡ መተቸታቸው የምርምር ግኝቶችን የሚያዳብር ሲሆን ተመራማሪዎችና መምህራን ሳይንሳዊ ግኝቶችን እንዲለዋወጡና የምርምር ጽሑፎቻቸውም ለማኅበረሰቡ ችግር መፍትሔ እንዲጠቁሙ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደገለፁት አውደ ጥናቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሠሩ ምርምሮች እየቀረቡ አስተያየቶች የተሰጡበትና በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ልምድ ልውውጥና የምርምር ጽሑፍ ዕውቀት የተገኘበት በመሆኑ ተመራማሪዎችና መምህራን በቀጣይ የዳበሩ ምርምሮችን በማዘጋጀት ኅብረተሰቡንና ሀገርን እንዲጠቅሙ በማድረግ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተሸመ ገለፃ ከ205 ጥናታዊ ጽሑፎች 46ቱ ተመርጠው የቀረቡ ሲሆን እነዚህም ከማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ከሕግና እና ከሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡና ለ2012 ዓ/ም ተዘጋጅተው በኮቪድ ምክንያት የተሻገሩ ናቸው፡፡

የጉባዔው ተሳታፊ ተመራማሪዎች በሰጡት አስተያየት በምርምር አውደ ጥናቱ ለወደ ፊት ጠቃሚ የሆኑ የምርምር ሃሳቦችን መለዋወጥ መቻላቸውን፣ የምርምር ግኝቶችን ወደ ማኅበረሰብ በማውረድ ሳይንሱን በመጠቀም ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል ዕውቀትና ልምድ ማግኘታቸውንና ከዚህ በኋላ የሚሠሩ ምርምሮች ወደ ማኅበረሰብ አገልግሎት ተቀይረው ያለውን ችግር እንዲፈቱ ለማድረግ ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ʻʻDemocratization and Peace in the Ethiopian State from 2018 to dateʼʼ በሚል ርዕስ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት መ/ር ሰለሞን ሞላ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ መሆኑና ለዴሞክራሲ ዕድገትም ከፍተኛ ተግዳሮች የተደቀኑ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በጥናቱ ውጤትም ኢትዮጵያ እስካሁን ያለፈችበትን ሁኔታ በአግባቡ በመረዳትና የጋሞ አባቶች ዓይነት ባህልን በመከተል ለችግሮች መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡

ሌላው ʻʻNurturing Sense of Institutional Soldier: Influence of Transformational Leadership Behaviors and Faculties Professional Commitmentʼʼ በሚል ርዕስ በደብረ-ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሰሙ ባጫ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲሁ የለውጡ አመራር፣ ከፍተኛና ዝቅተኛ ባለሙያዎች ከጊዜው ጋር ለመሄድ ማድረግ ስለሚገባቸው የመፍትሔ ሃሳብ እንዲሁም አመራሩና ሠራተኛ የለውጥ አራማጅና አርአያ መሆን እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በአውደ ጥናቱ 46 ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ʻʻDemocratization and Peace in the Ethiopian State from 2018 to dateʼʼ፣ ʻʻCorporate Branding and Communication Strategies Assessment of Ethiopian Higher Educationsʼʼ፣ ʻʻNurturing Sense of Institutional Soldier: Influence of Transformational Leadership Behaviors and Faculties Professional Commitmentʼʼ እና “Factors that Influence Child Labor and

Educational Participation Children in Public Primary Schools of Wolaita Zone” የሚሉት ከምርምር ጽሑፎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በዕለቱ ከ22 ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጋሞና ጎፋ ዞን 6 ሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ ከድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ዳይሬክተሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት