አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንሰቲትዩት ጋር በመተባበር በጋሞና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን የሚያሳይ ካርታ ለማዘጋጀት የሚያስችል ፕሮጀክት የሶስቱም ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ምሁራን በተገኙበት ቅዳሜ ሚያዝያ 16/2013 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ትራንስፎሜሽን ፕሮግራም ይደግፋልም ተብሏል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የቱሪዝም ዘርፍ እንደ ሀገር በተወጠነው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው 5 ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው መሰል ፕሮጀክቶች ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ ሚና ያበረክታሉ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ በተናጥልም ሆነ በትብብር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ለሀገሪቱ ዕድገትና ብልጽግና የሚጠበቅበትን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከወራት በፊት ከሁለቱ ተቋማት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ እንደነበር አስታውሰው የዚህም ፕሮጀክት ይፋ መሆን ስምምነታችን ከወረቀት አልፎ ወደ ተግባር እየተቀየረ ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ በሌሎች የስምምነት ዘርፎች ላይም በትብብር መሥራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

በዕለቱ የፕሮጀክቱን ንድፈ ሃሳብ ያቀረቡት የድኅረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻ እንደገለጹት ቱሪዝም በዓለማችን ከ200 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረና የዓለማችን 10 በመቶ ጂ ዲ ፒ መያዝ የቻለ ትልቅ ኢንደስትሪ ነው፡፡ የተዘጋጀው የፕሮጀክት ንድፈ ሃሳብም በሁለቱ ዞኖች ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችንና መሠረት ልማቶችን የሚያሳይ ካርታ የጂ አይ ኤስና ሪሞት ሴንሲንግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚዘጋጅበት ነው፡፡ በፕሮጀክቱ በሁለቱ ዞኖች የሚገኙ ባህላዊ፣ ሰው ሠራሽና ተፍጥሯዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በዝርዝር የሚያሳይ እንዲሁም በመዳረሻዎቹ ዙሪያና አቅራቢያ ያሉ የሆቴል፣ የመንገድ፣ ወዘተ. መሠረተ ልማቶች የሚካተቱበት መሆኑንም ዶ/ር አበራ ተናግረዋል፡፡

ካርታው ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በቀላሉ ተደራሽ የሚደረግ ሲሆን ለውጦችን ተከትሎ በየጊዜው በቀላሉ እየተከለሰ ለአካባቢው ቱሪዝም ዕድገት የራሱን ሚና እንደሚያበረክት ዶ/ር አበራ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ጄኔራል ዳይሬክተር ዶ/ር ቱሉ በሻ ፕሮጀክቱ ወቅታዊና የጂኦ ስፓሻል መረጃዎች ለቱሪዝሙ ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የሚያደርግ ሲሆን ተቋማቸው ለፕሮጀክቱ ስኬታማነትና በወቅቱ መጠናቀቅ አስፈላጊውን የፋይናንስ፣ የቁሳቁስና የሰው ኃይል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ቱሉ በፕሮጀክቱ ሌሎች በአካባቢው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችም በሂደት ተካተው ቢሠሩ ጠቃሜታው የጎላ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጄኔራል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው አርባ ምንጭና አካባቢው ትልቅ የቱሪዝም ሃብት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው አሁን የሚጀመረው ፕሮጀክት ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡ ተቋማቸው ለፕሮጀክቱ መጀመርና መጠናቀቅ የሚፈለግበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጄኔራል ዳይሬክተሩ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በ12 ወራት የሚጠናቀቅና ከ2.8 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የሚያስፈልገው ሲሆን ይህም በ3ቱ ተቋማት የሚሸፈን ይሆናል፡፡ በሂደትም ፕሮጀክቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሰፍቶ እንደሚሠራም ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት