አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጋሞ ዞን ገቢዎች ባለሥልጣን ቅ/ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከ12 ወረዳዎች ለተወጣጡ የICT ባለሙያዎች በኔትወርኪንግና በቢሮ ማሽኖች ጥገና ላይ ከሚያዝያ 14-19/2013 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረው የዚህ ዓይነት ሥልጠናዎችም የዚሁ ሥራ አካል ናቸው ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የጋሞ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ማቲዎስ ሥልጠናው ለተቋማችን ሠራተኞች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የተግባር ዕውቀት የሚያስገኝ እንዲሁም መሠረታዊ የሆኑ መጠነኛ ብልሽቶች ሲኖሩ መጠገን የሚያስችል ክሂሎት የሚያስጨብጥ ነው ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ሙሉጌታ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በርካታ የትብብር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረው ስልጠናው ባለሙያዎቹ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲገጥማቸው ችግሮቹን በራሳቸው እንዲፈቱ የሚያስችላቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመዝጊያ ንግግራቸው የተሰጠው ስልጠና ባለሙያዎቹ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከትንሽ እስከ ትልቅ ችግሮችን በራሳቸው እንዲፈቱ የሚያስችል መሆኑን ተናግረው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ መሰል ችፍር ፈቺ ሥልጠናዎችን መስጠቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በሥልጠናው መጨረሻም ለሠልጠኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት