የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የተፈጥሮ ሀብትና የምግብ ደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ፣ የዘላቂ መሬት አያያዝ ብሔራዊ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ኃይሉ፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሚያዝያ 23/2013 ዓ/ም በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዶ የጫሞ ተፋሰስን ለማዳን አስፈላጊው ሥራ በአፋጣኝ እንዲጀመር ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ IUC ፕሮጀክት አስተባባሪና በጋሞ ዞን የጫሞ ተፋሰስ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት የጫሞ ሐይቅን ለማዳን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት ጋር ከዚህ ቀደም በተፈራረሙት የጋራ ስምምነት መሠረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 6 ዋና ዋና እና ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮች ላይ ጥናት እንዲያካሂድና የአፈጻጸም ዕቅድ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት እንቦጭ አረምን ማስወገድ፣ በከፍተኛ ሁኔታ መንገዱን ጥሶ ወደ ፓርኩ በመፍሰስ የ40 ምንጮቹን ደን እያጠፋና አየር መንገዱን እያበላሸ ባለው የኩልፎ ተፋሰስ፣ በደለል ምክንያት የጠፋውን አዞ ገበያ ማዳን፣ በሐይቁ ዙሪያ ያሉትን የእርሻ ቦታዎች በመለየት ከውሃ ጋር የሚስማሙና የሚመጣውን አፈር መያዝ የሚችሉ ዕጽዋትን መለየት፣ የደን ጭፍጨፋ ምክንያቶችን በመለየት ለአካባቢው ማኅበረሰብ አማራጭ የሥራና የኃይል ምንጭ መፍጠር ላይ የጥናት ግኝትና የአፈጻጸም ዕቅድ ለውይይት ቀርቦ ከተገመገመ በኋላ ሐይቁን ለመታደግ የሚያስችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ተሟልተው ሥራው በአፋጣኝ እንዲጀመር ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር ዘላቂ የመሬት አያያዝ ልማት እስከ 100,000 ሄክታር ድረስ እንዲሠራ መወሰኑንና ሥራው በተጠናው ቦታ ላይ በታቀደው መልኩ መሠራቱን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ክትትል እንደሚያደርግ ዶ/ር ፋሲል ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ደለሉ የሚመጣው ከተፋሰሱ አናት ላይ በመሆኑ አናቱ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የጠፉ ደኖችን በቦታቸው የመመለስ፣ አገር በቀል ዕጽዋትን የመትከል፣ ወንዞቹ አፈር ይዘው እንዳይወጡ የመከላከል፣ እርከንና ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት በውይይት እንደሚወሰንም ተናግረዋል፡፡

ጫሞ ሐይቅን ለመታደግ የሁሉም ሰው ከፍተኛ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ፋሲል ተናግረው የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን መምጣት ሐይቁን ለማዳን በዞን ደረጃ የጀመርነውን ትስስር ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን ሐይቁን ለመታደግ የበኩላቸውን ላበረከቱ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት