አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገ የእንሰት ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ ወድድር በኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት በተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ተወዳድሮ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንደገለጹት በውድድሩ በሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት እና የቴክኒክና ግብርና ኮሌጆች የተወጣጡና በዘርፉ የፈጠራ ሥራ ያላቸው ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን ውድድሩ በሦስት ዘርፎች ማለትም በእንሰት መፋቂያ፣ ማብለያና ከእንሰት በተሠሩ እሴት የተጨመረባቸው ምግቦች በተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ላይ የተደረገ ነው፡፡ በውድድሩ በሦስቱም ዘርፎች አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አሸናፊ በመሆን የዋንጫና የምስክር ወረቀት በመሸለም ዕውቅና አግኝቷል፡፡

እንደ ዶ/ር አዲሱ ገለጻ ውድድሩ በዋናነት በዘርፉ ከተሠሩ ቴክኖሎጂዎች የተሻሉትን በመለየት ዕውቅና መስጠትን ዓላማ ያደረገ ሲሆን የቴክኖሎጂዎቹ ለአጠቃቀም ምቹ መሆን፣ ዋጋቸውና ውጤታማነታቸው የውድድሩ ዋነኛ መስፈርቶች ናቸው፡፡ በመስፈርቶቹ መሠረት በዩኒቨርሲቲው የቀረቡት የእንሰት መፋቂያ፣ የእንሰት ማብላላት ሂደትን ከጉድጓድ ውስጥ የሚያወጣ ከሴራሚክ የተሠራ እንስራና ሂደቱን የሚያፋጥን እርሾ እንዲሁም ከእንሰት የተሠራ ድፎ ዳቦ፣ ኬክና ኩኪስ ቴክኖሎጂዎች የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው አሸናፊ መሆን ችለናል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የገንዘብ ድጋፍ ሲከናወን መቆየቱን ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

ዕውቅናው ለቀጣይ ሥራ ትልቅ የሞራል ስንቅ የሚሆንና የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳ አደራም ጭምር መሆኑን ዶ/ር አዲሱ ተናግረው ለስኬቱ የፕሮጀክቱ አባላትና የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ትልቅ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ለሚሠሩ ቴክኖሎጂዎችና በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ እንሰት አብቃይ አካባቢዎች የተገኘውን የምርምር ውጤት የማዳረስ ሥራ ላይ የዩኒቨርሲቲው በትኩረት ሊደግፈን ይገባል ብለዋል፡፡

ዶ/ር አዲሱ የ3ኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፋቸው እ.ኤ.አ በ2020 በአውሮፓ ከተሠሩ የ3ኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ምርምሮች መካከል 1ኛ ደረጃን በማግኘት ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት