የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እና የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጆች የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ከጋሞ ዞን ፕላን መምሪያ ጋር በመተባበር ለዕቅድና ፕላን ባለሙያዎች ‹GIS› እና ‹STATA› የተሰኙ የቦታ መረጃ አያያዝና ዘመናዊ የበጀት ቀመር አሠራር ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከግንቦት 09-13/2013 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሹሬ እንደገለጹት ሥልጠናው ባለሙያዎቹ መረጃዎችን በፎቶ፣ በቪዲዮና በካርታ አደራጅተው በኮምፒውተር እንዲይዙ የሚረዳቸው ነው፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ በበኩላቸው ሥልጠናው ባለሙያዎች በተሻለና በተቀላጠፈ ሁኔታ ውጤታማ ሥራ እንዲሠሩ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ ሶፍትዌር ተደግፎ የበጀት ቀመር ሲሠራ በተለያዩ ጊዜያት በበጀት ክፍፍል ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ ጭቅጭቅና ሃሜቶችን ያስቀራልም ብለዋል፡፡

የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል ረ/ፕ ዓለሙ አሰሌ በበኩላቸው የዕቅድና ፕላን ኮሚሽን አዲስ የተቋቋመ በመሆኑ ሥልጠናው የመሬት፣ የልማት ተቋማት፣ የደንና የግብር መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀት፣ በመተንተንና ተግባራዊ ማድረግ ላይ የባለሙያዎችን ክሂሎት ያሳድጋል፡፡

በጋሞ ዞን ፕላን መምሪያ የሶሺዮኢኮኖሚና ፊዚካል ጂኦግራፊ ትንተናና ጥናት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ድጊሴ ደበታ ሶፍትዌሮቹ መረጃን በአግባቡ ለመያዝ የሚያስችሉ በመሆናቸው ሥልጠናው በጣም አስፈላጊና መረጃን አጥርተን ለመሥራት የሚያግዘን ነው ብለዋል፡፡

በመምሪያው የመረጃ ሥራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ኪዳን ሞላ በበኩላቸው ለሚሠሩት ሥራ መነሻ የሚሆን ጠቃሚ ክሂሎት ማግኘታቸውን ተናግረው በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ ጋር ተናቦ ሰፋ ያለ አቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ቢሰጠን በሥራችን ውጤታማ እንድንሆን ይረዳናል ብለዋል፡፡

መረጃ አያያዝ፣ አደረጃጀት፣ አተናተን እንዲሁም ካርታ አዘገጃጀትና አጠቃቀም በሥልጠናው ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ የግብርና፣ የፋይናንስ ልማት እና የከተማና ገጠር ልማት ባለሙያዎች እንዲሁም የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡ በሥልጠናው መጨረሻም ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት