የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ በጫሞ ካምፓስ አካባቢ ካሉ ነጋዴዎች ጋር በወጣት ተማሪዎች ስብዕና ግንባታና የነጋዴው ማኅበረሰብ ባለው ሚና ዙሪያ ግንቦት25/2013 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሹሬ ከዚህ ቀደም መሰል የውይይት መድረኮች መዘጋጀታቸውን አስታውሰው መድረኩ የሱስ አስከፊነትን በማስገንዘብ የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥሩ ዜጋን ለማፍራት ኃላፊነቱ ምን መምሰል እንዳለበት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የክሊኒካል ሳይኮሎጂ መምህርት ኑሃሚን የኔሰው እንደገለጹት በካምፓሶች ዙሪያ የሱስ ቤቶች መበራከት ተማሪዎች ወደ ሱስ እንዲገቡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ አደንዛዥ ዕጾች ተማሪዎች ላይ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተጽዕኖዎች እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ጫናዎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ግንዛቤ ለማስፋትና ተማሪዎቹን እንዲታደጋቸው ለማሳሰብ የውይይት መድረኩ ተዘጋጅቷል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ በበኩላቸው በመድረኩ ለወጣቱ የሥነ-ምግባር ጉድለት ምክንያት የሚሆኑ እንደ ጫት፣ መጠጥ፣ ሲጋራ፣ ሀሺሽና ሺሻ የመሳሰሉ አደገኛ ዕጾች ዙሪያ የተሠሩ ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸውን ገልጸው ከተሳታፊዎች አስተያየት መሰብሰቡን፣ ለቀጣይ ሥራዎች አቅጣጫ መቀመጡንና የሱስ ቤቶችን ለማጥፋት ከመንግሥት እስከ ታች ያለው ማኅበረሰብ በቅንጅት መሥራት እንዳለበት ከመግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ተወያዮች በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋሉ የቁጥጥር ማነስ፣ የመምህራን ሥነ-ምግባር፣ የወላጅ ክትትል አለመኖርና የነጋዴው በኃላፊነት አለመሥራት ለችግሩ መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላትና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

በውይይቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የቀበሌው የጸጥታ አካላትና በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት