የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ሰኔ 14/213 ዓ/ም ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መልስ በዋናው ግቢ የችግኝ ተከላ በማካሄድ አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በአርባ ምንጭ ከተማ ነጭ ሳር ክ/ከተማ ውሃ ምንጭ ቀበሌ መምረጣቸውን ገልጸው ከምርጫ ቦርድ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካለት የተቀናጀ ሥራ በመሥራታቸው ምርጫው ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡ የሀገራችንን የአረንጓዴ ልማት አሻራ ከግብ ለማድረስና ለዜጎች ምቹ መኖሪያ ከማድረግ አኳያ የ3ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንደሚካሄድም ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ረ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በአርባ ምንጭ ከተማ ጫሞ ቀበሌ መምረጣቸውን ተናግረው በዲሞክራሲያዊነቱና በአሳታፊነቱ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንደመረጠ መመልከታቸውን የገለጹት ረ/ፕ በኃይሉ እንደ ሀገርም ሆነ በከተማችን ገዢው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቀራርበው በመሥራት ያሳዩት አንድነት የሚያስደስት መሆኑንና የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበል እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው ግቢና በመኖሪያ አካባቢዎች የተተከሉትንም ሆነ በምርጫው ዕለት የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

በምርጫ ስሳተፍ 3ኛ ጊዜዬ ነው ያሉት የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ምርጫው ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ ሰላማዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በ3ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና ምርጫውን አስመልክቶ የተለያዩ ችግኞችን ተክለናል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት