የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት በዘርፉ የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ንድፈ ሃሳቦች የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዙር ግምገማ መስከረም 8/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ለግምገማ የቀረቡት 30 የምርምር ንድፈ ሃሳቦች ሲሆኑ አብዛኛዎቹ በሀገረሰብ ዕውቀቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

የግምገማው ዓላማ የጥናትና ምርምር ንድፈ ሃሳቦችን በመስኩ ባለሙያዎች በማስገምገም የአካባቢውን ብሎም የአገሪቱን ችግር በተገቢው ሁኔታ ይፈታሉ ተብለው የሚታመንባቸውንና መስፈርቱን የሚያሟሉትን መለየት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አህመድ ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቀረቡት የጥናትና ምርምር ንድፈ ሃሳቦች ከቋንቋ፣ ታሪክ፣ ሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ፣ ሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር፣ ቱሪዝም እና ጂኦግራፊ ት/ክፍሎች የተወጣጡ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ግምገማ ያላለፉት ከገምጋሚዎች የተሰጡትን የማሻሻያ አስተያየቶች ተቀብለው በማጠናከር እንዲቀርቡ የሚደረግ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የጥናትና ምርምር ንድፈ ሃሳብ ካቀረቡት መምህራን መካከል ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ት/ክፍል ተ/ፕ አባተ ደምሴ ያቀረቡት የምርምር ንድፈ ሃሳብ የተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ የብቃት ደረጃ በክፍል ውስጥ የተለያዩ ሥልቶችን በመጠቀም አቻችሎ የማስተማር ዘዴ፣ የመምህሩ ግንዛቤና የክፍል ውስጥ አተገባበር ላይ ያተኩራል፡፡ የተማሪዎቹ የቋንቋ አጠቃቀም ደረጃ መለያየት በውጤታቸው ላይ ስላለው አስተዋጽኦ ምርምሩ ምላሽ እንደሚኖረው ተ/ፕ አባተ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሪት እመቤት ደመላሽ በሐመር አካባቢ በሴቶች ግርፊያ ላይ ያጠነጠነ የፊልም ፕሮፖዛል ያቀረቡ ሲሆን ዋነኛ ትኩረቱ ግርፊያው እንዲቀጥል ያስቻለውን ትክክለኛ ምክንያት፣ በሴቶቹ እና በመንግሥት ረገድ ያለውን አመለካከት፣ ባህላዊ ትውፊቱን እንዲሁም ከቱሪስት መስህብነት አንፃር ያለውን ፋይዳ መለየት ነው ብለዋል፡፡ ይህም ባህላዊ ልማዶችን መረጃ አድርጎ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የፎክሎርና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ዶ/ር ተመስገን ምንአውጋው በሙያ መስካችን አካባቢን መሠረት ያደረጉና ለኅብረተሰቡ እድገት የሚበጁ ጥናቶችን በማጥናት ወደ ማኅበረሰቡ ደርሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የተሻሉ ነገሮችን ወደ ማኅበረሰቡ በማድረስ አድካሚ ከሆነ ባህላዊ የአሠራር መንገድ በማላቀቅ ወደ ጎጆ ኢንደስትሪ ማበልጸግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹የደራሼ ቋንቋ የቃል ክፍሎች››፣ ‹‹የቅድስና እሳቤና እምነቶች በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ያላቸው ሚና እና የሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች በደቡብ ኢትዮጵያ ጋሞ ዞን››፣ ‹‹የዘይሴ ብሔረሰብ ባህላዊ የሰርግ ሥነ-ሥርዓት ክዋኔ››፣ ‹‹የባህላዊ ኢኮኖሚያዊ ዕውቀት ሥርዓት የአየር ንብረት ለውጥን ለመላመድና ለመቋቋም ያለው ፋይዳ ግምገማ በጋሞ ደጋማ እና በደቡብ ኦሞ ቆላማ አካባቢዎች››፣ ‹‹ወጌሻ፡- ሀገር በቀል የቴራፒ ዕውቀት ሽግግርና በጡንቻና አጥንት ጉዳቶች ላይ ያለው ውጤታማት››፣ ‹‹በኢትዮጵያ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የተለጠፉ ሥነ-ቃሎች የትራፊክ ደኅንነትን ከማስጠበቅ አንጻር ያላቸው ፋይዳ›› እና ሌሎችም የምርምር ንድፈ ሃሳቦች ቀርበው ተገምግመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት