‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት›› መርሃ-ግብር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ መስከረም 21/2014 ዓ/ም በማዕከል ደረጃ ተካሂዷል፡፡ በቀጣይ ቀናት መርሃ-ግብሩ በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ  

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ሀገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከታላቁ ህዳሴ ግድብና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከአሸባሪው የሕወሓትና ተላላኪዎቹ ጋር እየተደረገ ካለው የሕልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ጫናና ጣልቃ ገብነት እየተካሄደባት ይገኛል ብለዋል፡፡ ይህንን በሀገራችን ላይ እየተካሄደ ያለውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የዩኒቨርሲቲያችን ማኅበረሰብ ፐብሊክ ዲፕሎማት በመሆን የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ለሀገሩ ድምጽ በመሆን እውነታውን ዓለም እንዲገነዘብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት›› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው መርሃ-ግብር የዚሁ ድምፃችንን የምናሰማበት አንዱ መንገድ ስለሆነ የዩኒቨርሲቲያችን መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች በፕሮግራሙ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ፕሬዝደንቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ በበኩላቸው አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች መስፋት ጋር ተያይዞ የዲፕሎማሲ ሥራ ተቋማዊ መሆኑ ቀርቶ ሕዝባዊ መሆኑና የሕዝብ አስተያየትም ከፍ ያለ ተጽዕኖ የሚፈጠርበት መሰክና ጉልህ ሚና ያለው እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡ ከዚህም አንፃር ሁላችንም ‹‹እኔም የሀገሬ ዲፕሎማት ነኝ!›› በሚል መሪ ቃል ሀገራችን ላይ የተከፈተባትን የሚዲያና የዲፕሎማሲ ጫና ለመከላከል እንደ "Twitter" ያሉ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ከመርሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች መከከል አስተያየታቸውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የመረጃና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ታደሰ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል በዩኒቨርሲቲያችን መመሥረቱ ሥራው ተቋማዊ ሆኖ በተደራጀ ሁኔታ እንዲሠራ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረው ለማዕከሉ መጠናከርና ስኬት ዳይሬክቶሬታቸው እንደ ሥራው ባለቤት የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም እንደ "Twitter" ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን በመክፈት በሚደረጉ ዘመቻዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን ያለመታከት ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ተ/ፕ ወይንእሸት ወልደፃዲቅ በበኩላቸው መርሃ-ግብሩ በሁሉም ካምፓሶች መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ዘርፍ ሠራተኞች እንዲሳተፉ ተደርጎ ድምፃችንን በማሰማት ሀገራችንን እየደረሰባት ካለው የዲፕሎማሲና የሚዲያ ጫና ልንከላከል ዘብ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ አስተባባሪዎች፣ የተማሪዎች ተወካዮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

 

       የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት